ለሕብረት ሥራ ማኅበራቱ የተመቻቸው የ500 ሚሊዮን ብር ብድር የምርት አቅርቦታቸውን አሳድጎታል

102

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7/2013 (ኢዜአ) የኅብረት ሥራ ማኅበራት በመዲናዋ ገበያ ለማረጋጋት በተመቻቸላቸው የ500 ሚሊዮን ብር ብድር ተጠቅመው የተለያዩ ምርቶችን ለገበያ እያቀረቡ መሆኑ ተገለፀ።

የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ የሚስተዋለው የማያቋርጥ የዋጋ ጭማሪ የዜጎችን የመኖር ህልውና ፈተና ውስጥ ከቶታል።

መንግስትም ችግሩን ለማቃለል የግብርና ምርቶችን በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ለዜጎች በማቅረብ ላይ ይገኛል።

ይሁንና የግብርና ምርቶችን በብዛት ገዝቶ ለኅብረተሰቡ ለማድረስ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ሆኖ ቆይቷል ይላሉ የፌዴራል ሕብረት ሥራ ማኀበራት ኤጀንሲ የኅብረት ሥራ ግብይት ዳይሬክተር ወይዘሮ ይርጋለም እንየው።

የፋይናንስ ችግሩን ለመፍታት መንግስት እርምጃ እየወሰደ መሆኑንና የአዲስ አበባ አስተዳደርም በቅርቡ ለኀብረት ሥራ ማኅበራት የ500 ሚሊዮን ብር ብድር መፍቀዱን ጠቅሰዋል።

የገንዘብ ብድር መፈቀዱን ተከትሎ የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ የተለያዩ ምርቶችን በማቅረብ ገበያውን እያረጋጉ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ማኅበራቱ አቅርቦታቸው እንዳይስተጓጎል ከልማት ባንክ ብድር ተመቻችቶላቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ ነው።   

በዚህም የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተሻለ ሁኔታ ለማኀበረሰቡ እያቀረቡ እንደሆነ ነው የገለጹት።

በቅርቡ በመዲናዋ በተካሄደ ኤግዚቪሽን ከተለያዩ ክልሎች የመጡ አቅራቢዎች በቀጥታ ከሸማቹ ጋር እንዲገናኙ መደረጉንና ይህም ገበያውን ለማረጋጋት አስተዋጽኦ ማበርከቱን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

እንደ ወይዘሮ ይርጋለም ገለጻ፤ የገበያ አለመረጋጋት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በግብይት ስርዓቱ የማያስፈልጉ ሰንሰለቶችን በመቁረጥ ሸማችና አምራቹ በቀጥታ የሚገናኙበት ስርዓት መቀየስ ቁልፍ ጉዳይ ሊሆን ይገባል።  

ከዚህ ጋር በተያያዘ አምራች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በተለይም በትላልቅ ከተሞች ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለሸማቹ የሚያቀርቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።  

ዳይሬክተሯ በአዲስ አበባ ዋና ዋና መግቢያ በሮች ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት ለመገንባት የፋይናንስ ማፈላለግ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም