የቴክኒክና ሙያ ስልጠና የህብረተሰቡን ችግሮችን ለመፍታት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እያሳየ ነው – ዶክተር አብርሐም በላይ

375

አዳማ ፤ ሚያዝያ 7/2013 (ኢዜአ) የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና የህብረተሰቡን ችግሮች በመፍታት ረገድ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እያሳየ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሐም በላይ ገለጹ፡፡

የኦሮሚያ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ቢሮ በአዳማ ከተማ ከሚያዚያ 4/2013ዓ.ም ያዘጋጀው ባዛርና የእውቅና ሽልማት አሰጣጥ ስነ-ስርዓት ትናንት ተጠናቋል።

በማጠቃለያ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሐም በላይ እንዳሉት፤ የሀገሪቱ የቴክኖሎጂ ፍላጎትን በመረዳት ክፍተቱን ለመሙላት በሚደረገው ጥረት ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት አሁንም መጠናከር አለባቸው፡፡

በተለይም ወጣቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ላይ በማተኮር ከሰሩ ከራሳቸው አልፎ የህብረተሰቡም ኑሮ ይቀየራል፤ የእለት ተእለት ችግሮችም ይፈታሉ  ብለዋል።

የቴክኒክና ሙያ ተማሪዎችና የዘርፉ መምህራንም ጊዜያቸውን በምርምርና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ በማሳለፍ  ወደ ብልፅግና ለመሻገር የሚደረገውን ጉዞ መደገፍ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ይህም ሆኖ በእስካሁኑ ሂደት ቴክኒክና ሙያ ትምህርት የህብረተሰቡን ችግሮች በመፍታት ረገድ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እያሳየ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። 

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው ያደጉ ሀገራትን ተሞክሮ ሲታይ ከመሬት ተነስተው ሳይሆን በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በፈጠራ ስራ ላይ አተኩረው በመስራታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ ተስፋ አላት ስንል ዛሬ ላይ የምናነሳቸውን ጥቃቅን ችግሮች ወደ ኋላ የሚመልሱን ሳይሆኑ የፈጠራ ችሎታችንን ተጠቅመን ልንሻገራቸው የሚገቡ ናቸው ” ብለዋል።

የክልሉ መንግስትም የፈጠራ ግኝቶች ተስፋፍተው የህብረተሰቡን ህይወት እንዲቀይሩ የፋይናንስ ድጋፍና  የመስሪያና መሸጫ ቦታዎችን ያመቻቻል ሲሉም አስታውቀዋል ። 

የኦሮሚያ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኤባ ገርባ ፤ ዘንድሮ ከ1 ሺህ 200 በላይ ፈጠራዎች ተሻሽለው በመሰራት ለማህብረሰቡ መሰራጨታቸውን አውስተው ፤ ለወደፊቱም ቢሮው በመስኩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

በማጠቃለያ ስነ-ስርዓቱ  በልዩ ልዩ ፈጠራዎች ላይ የጎላ አስተዋዕኦ ላደረጉ  ከ140 በላይ መምህራንና ተማሪዎች የምስክር ወረቀትና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።