የኢትዮጵያ ካራቴ ሻምፒዮና ውድድር በአማራ ክልል አሸናፊነት ተጠናቀቀ

ደሴ ፤ሚያዚያ 7/2013 (ኢዜአ) በደሴ ከተማ ሲካሄድ የሰነበተው የኢትዮጵያ ካራቴ ሻምፒዮና ውድድር በአማራ ክልል አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ ።

ከሚያዚያ 2/2013 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የነበረውና ትናንት በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ካራቴ ሻምፒዮና ውድድር የአማራ ክልል አንደኛ በመውጣት አሸናፊ የሆነው ዘጠኝ የወርቅ ሜዳሊያና አምስት ዋንጫ በመሰብሰብ ነው።

ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሦስት የወርቅ ሜዳሊያና አንድ ዋንጫ ሁለተኛ፤ አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ በአንድ ወርቅና አንድ ዋንጫ ሶስተኛ ደረጀን ይዘው አጠናቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰፋ አንጅሎ በማጠቃለያው ስነ-ስርዓት እንደገለጹት፤ በውድድሩ ከሰባት ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስዳደሮች የተውጣጡ 110 ስፖርተኞች ተሳትፈዋል፡፡

ውድድሩ የካራቴ ስፖርትን ለማሳደግና በህዝብ ዘንድ የተሻለ እውቅና እንዲኖረው ለማስቻል ብሎም ተተኪ ስፖርተኞች ለማፍራት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

በግብፅ ካይሮ በነሃሴ ወር 2013 ዓ.ም ለሚካሄደው የአፍሪካ ካራቴ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉ 12 ስፖርተኞችም መመረጣቸውንም አስታውቀዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ካራቴ ልዑካን ቡድን አስተባባሪ አቶ ሳዲቅ ከማል በሰጡት አስተያየት ውድድሩ የኢትዮጵያን አንድነትና የሰላም  እሴት ለማጎልበት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

የውድድሩ አሸናፊ ለመሆን በቂ ዝግጅት ቢደረግም ውድድር ነውና ሁለተኛ ደረጃ በመውጣታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ቀጣይ ኢትዮጵያን ወክለው ለአፍሪካ ካራቴ ሻምፒዮና የሚወዳደሩ ስፖርተኞችም የሀገሪቱን ባህልና ወግ ማስተማር እንደሚኖርባቸውም ጠቁመዋል።

ውድድሩ አንድነትና ሰላማችንን ከማስጠበቅ ባለፈ የካራቴ ስፖርት እንዲጎለብት ያደርጋል ያለው ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተሳታፊ ወጣት በእድሉ አብደላ ነው፡፡

በውድድሩ የእርስ በርስ ግንኙነታችን አጠናክሮልናል ያለው ወጣቱ በተለይ በወሎ ማዕከል ደሴ ከተማ መካሄዱ ፍቅርን፣ ሰላምንና አብሮነት እንዲጎለብት  ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግሯል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም