በኢትዮጵያ የመጀመሪያው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አውደ ርዕይ እየተካሄደ ነው

109

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7 /2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሰው ሰራሽ አስተውሎት /አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ/ አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሰው ልጅ በተፈጥሮና በህይወት ዑደት የሚያገኛቸውን የማሰብ፣ መገንዘብ ማመዛዘን፣ ማቀድ፣ ምክንያታዊ የመሆን የመማርና በቋንቋ የመግባባት ክህሎትን በረቀቀ ቀመር ማሽኖችን በማስተማር የተለያዩ አይነት ተግባራትን ማከናወን የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡

ኢትዮጵያም ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ ፍይናንስ፣ ትራንስፖርት ሚትዎሮሎጂ፣ ኤሮስፔስ እና ሌሎች ዘርፎችን ገቢራዊ ለማድረግ ስራውን ጀምራለች።

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 463/2012 የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል መንግሥታዊ መስሪያ ቤት ሆኖ እንዲቋቋም የተደረገ ሲሆን መስከረም 2013 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ተመርቆ በይፋ ስራ መጀመሩም ይታወቃል።

ማዕከሉ ሀገር አቀፍ ምርምርና ልማት ማዕከል በማቋቋም የመለኪያ መስፈርቶችን በማዘጋጀት የዲጂታል ዳታ ክምችትን በጥራት እያከናወነ ይገኛል።

በተለያዩ የልማት ዘርፎች በተለይም በፋይናንስ ዘርፍ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምረው ወደ ምርት ደረጃ የተሸጋገሩ በምስለ ምርት ደረጃ ያሉና በሙከራ ላይ የሚገኙ ስራዎች በማዕከሉ እንደሚገኙ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አውደ ርዕይም ዛሬ በአዲስ አበባ በይፋ የተጀመረ ሲሆን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ዑርቃቶ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብረሃም በላይ እንዲሁም ሌሎች ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚቆየው አውደ ርእይ "አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለሁሉም" በሚል መሪ ሃሳብ ይከናወናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም