የቴአትር ጥበብ የተዳከመው በመንግሥትና በዘርፉ ባለሙያዎች ጭምረ ትኩረት በማጣቱ ነው - የቴአትር ከያኒያን

97

ሚያዚያ 6/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የቴአትር ጥበብ የተዳከመው ከመንግስት በተጨማሪ የዘርፉ ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተው ባለመስራታቸው ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቴአትር ከያኒያን ወቀሱ።

በኢትዮጵያ ቴአትር የተጀመረበትን 100ኛ ዓመት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዘርፉ እንዲነቃቃ ማድረግ እንደሚቻልም ገልፀዋል።

ለኢትዮጵያ ቴአትር አጀማመር የዘመናዊ ትምህርት መጀመር፣ የተለያዩ የህትመት ሥራዎች መስፋፋትና ዘመናዊንትን የመሻት ስሜት አስተዋፅኦ እንደነበረው የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ።

በበጅሮንድ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም ተዘጋጅቶ ለመጀመሪያ ግዜ ዘመናዊ ቴአትር ለዕይታ ከበቃ በኋላ ደግሞ ቴአትር እና ቴአትር ቤቶች ተስፋፋተዋል።

ዘርፉ የተለያዩ ሂደቶችን በማለፍ ከተጀመረ የአንድ ምዕተ ዓመት ዕድሜ ቢያስቆጥርም የዕድሜውን ያህል አለማደጉን የዘርፉ ከያኒያን ይናገራሉ።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ እጅግ እየተዳከመ መምጣቱን ነው የሚያነሱት። 

ለዚህም ከመንግስት በተጨማሪ የቴአትር ባለሙያዎች ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው አለመስራታቸውን እንደ ምክንያት ያነሳሉ።

የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አብዱልከሪም ጀማል መገናኛ ብዙሃንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከቴአትር ይልቅ ለሌሎች ዘርፎች ትኩረት መስጠታቸው ለዘርፉ መዳከም ምክንያት ነው ይላሉ።

ይሁንና የቴአትር ጥበብ የተጀመረበት መቶኛ ዓመት መከበር ለዘርፉ መነቃቃት ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።

በ'ቀንዲል ቤተ-ተውኔት' ተዋናይ የነበረው ነፀረ ሀብተወልድ በበኩሉ ቴአትር በመንግሥት ትኩረት ስላልተሰጠው ተዳክሟል ባይ ነው።

ከቴአትር ይልቅ ፊልሞች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሰራቱ ዘርፉ እንዳያድግ እክል እንደፈጠረበት የገለጹት ደግሞ የራስ ቴአትር ተዋናይ ታሪኩ ምትኩ ነው።

 ባለሙያዎቹ ቴአትር በኢትዮጵያ የተጀመረበትን መቶኛ ዓመት በመጠቀም ባለሙያዎችና ተመልካቹን ማነቃቃትና ዓለም አቀፍ የቴአትር ተሞክሮዎችን መውሰድ እንደሚገባም ገልፀዋል።

ቴአትርን በቴአትር ቤቶች ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ ያለበት ድረስ በመውሰድ ማሳየት እንደሚገባም አመልክተዋል።

መንግስትና ባለሃብቱ ይህን የጥበብ ዘርፍ በኢኮኖሚ እንዲደግፉም ነው ባለሙያዎቹ ጥሪ ያቀረቡት።

የቴአትር ባለሙያዎች ለቴአትር ጥበባት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸውም እንዲሁ።

በኢትዮጵያ ቴአትር የተጀመረበት 100ኛ ዓመት "ቴአትርን ማነቃቃት" በሚል መሪ ሀሳብ በቴአትር ባለሙያዎች አዘጋጅነት ትናንት በአዲስ አበባ ተዘክሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም