ቦርዱ የመራጮች ምዝጋባ ሂደትን አስመልክቶ ከፓርቲዎች ጋር ተወያየ

65

ሚያዚያ 6/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እየተካሄደ የሚገኘውን የመራጮች ምዝገባ ሂደት አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር ውይይት አደረገ።

የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከተወካዮቹ ጋር ባደረጉት ውይይት የተሰሩ ስራዎችና ያጋጠሙ ችግሮችን አንስተዋል።

ሰብሳቢዋ እንደገለጹት በአገሪቱ ወደ ስራ መግባት ካለባቸው 50 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች 25 ሺህ 151 የሚሆኑት ወደ ስራ ገብተዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ያጋጠመ የሰላም መደፍረስ፣ የተፈናቀሉ ወገኖች ያሉባቸው አካባቢዎች የተጣራ መረጃ ያለመቅረብ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁስ በማጓጓዝ ወቅት ያጋጠመ የትራንስፖርት እጥረትና ሌሎችም የምርጫ ጣቢያዎችን በወቅቱ ለመክፈትና የቁሳቁስ ስርጭት ለማድረግ እንቅፋት መሆናቸውን አስረድተዋል።

የአፋር እና የሶማሌ ክልል እስካሁን ባለው ሂደት የመራጮች ምዝገባ ማካሄድ ያልጀመሩ ሲሆን ሌሎች ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ስራ እየጀመሩ ነው ብለዋል።

ይህ ሁኔታ ተደማምሮ የመራጮች ምዝገባ እንዲቀዛቀዝ ምክንያት መሆኑንና አነስተኛ ቁጥር ያለው ሰው የምርጫ ካርድ መውሰዱን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የመራጮች ምዝገባ ከተመጀረ አንስቶ እስካሁን ወደ 200 ሺህ ገደማ ነዋሪ የመራጭነት ካርድ መውሰዱን ገልጸዋል።

ቦርዱ እስካሁን መልካም በሚባል ሁኔታ የምርጫ ሂደቱን እየመራ መሆኑን ገልጸው ችግር ባለባቸው አካባቢዎች እንደ ሁኔታው ችግሩ እየተፈታ፤ የሚሻሻለው እየተሻሻለ ለምርጫው የሚደረገው ዝግጅት ይቀጥላል ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችም በገዥው ፓርቲ እስርን ጨምሮ የተለያዩ ጫናዎች እየደረሱብን ነው ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል።

የምርጫ ጣቢያዎች መራጮችን መመዘገብ አለመጀመራቸው አሳሳቢና ሁሉም ሊረባረብበት የሚገባ ነው ብለዋል።

የተወሰኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ተወካዮችም የባከነው የመራጮች ምዝገባ ጊዜ በምን መልኩ መካካስ እንዳለበት በግልጽ እንዲቀመጥ ሲሉ ጠይቀዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዱአለም በበኩላቸው ፓርቲው የተሻለ ምርጫ እንዲካሄድ እየሰራ ነው ብለዋል።

ፓርቲው የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት መታሰር እንደሌለባቸው ያምናል በማለት፤ ችግሮች ሲያጋጥሙ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየተነጋገረ እየፈታ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመወቃቀስ ይልቅ መተባበር ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ የጠቀሱት አቶ ብናልፍ በተፎካካሪዎች በኩልም የተለያዩ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

የመራጮች ምዝገባ ከመጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም