በመንግስት ተሽከርካሪ የኮንትሮባንድ ዕቃ ጭኖ ሲጓዝ የነበረ አሽከርካሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ

59

ነገሌ፤መጋቢት 6/2013 (ኢዜአ) በጉጂ ዞን ለምርጫ አስፈጻሚዎች የተመደበና የዞኑ ጤና ጽሕፈት ቤት ንብረት በሆነ ተሽከርካሪ የኮንትሮባንድ እቃ ሲያጓጉዝ የነበረን አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ገለጸ፡፡

በመምሪያው የወንጀል መከላከል ሃላፊ ዋና ሳጂን ጉተማ ሳፋዬ እንዳሉት የተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች 24 ኢንች በጸሐይ ሃይል የሚሰሩ 20 ኤልኢዲ ፍላት እስክሪን ቴሌቭዥኖች ናቸው፡፡

የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 4-05370 ኦሮ የሆነው ተሽከርካሪ ለወረዳ ምርጫ አስፈጻሚዎች ከመንግስት የተመደበ የዞኑ ጤና ጥበቃ ንብረት እንደነበርም ዋና ሳጂን ጉተማ ገልጸዋል፡፡

ፖሊስ ባደረገው ክትትል ተሽከርካሪው የተመደበበትን አላማ ስቶ የኮንትሮባንድ እቃ ከቦረና ዞን ኤሬሮ ወረዳ ጭኖ ሻኪሶ ከተማ ሲደርስ ሚያዝያ 4 ቀን 2013 ዓ.ም በቁጥጥር ሥር መዋሉን ተናግረዋል።

በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የተገኘውና 129 ሺህ 200 ብር የሚገመተው የኮንትሮባንድ ዕቃም ለነገሌ ገቢዎችና ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ገቢ መደረጉንም ሃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ለታላቅ ሀገራዊ ስራ ተመድቦ አላማውን በመሳት በህገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርቶ መገኘቱ እንግዳና አዲስ ነገር ሆኖብናል ያሉት ዋና ሳጂን ጉተማ፤  በወንጀል ድርጊቱ ከአሽከርካሪው በተጨማሪ ንብረቶቹ የኔ ናቸው ያለችው አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር መዋሏን አስረድተዋል።

ፖሊስ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴንና የጸጥታ ስጋቶችን ለመከላከል ጥብቅ ክትትል በማድረግ ላይ እንደሆነ አመልክተው፤ ተጠርጣሪዎቹ በህግ ጥላ ስር ሆነው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በህገ ወጥ እንቅስቃሴ ላይ ተሰማርቶ የተገኘ ማንም ይሁን ማን ተጠያቂ ስለሚሆን ከወዲሁ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትና ህብረተሰቡም ጥቆማ እንዲሰጥ ሃላፊው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም