የሎጎና አርዲፖ ሃይቆች ከሰው ሰራሽ ችግር ለመታደግ በጥናት የተደገፈ የመፍትሄ ሀሳብ ቀረበ

88

ባህርዳር ፤ሚያዚያ 6/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙት የሎጎና አርዲፖ ሃይቆች በሰው ሰራሽ ችግር እየደረሰባቸው ካለው ጉዳት በዘላቂነት ለመታደግ የወሎ ዩኒቨርሲቲ በጥናት የተደገፈ የመፍትሄ ሀሳብ አቀረበ።

ሃይቆችን ከጥፋት ለመታደግ በሚቻልበት ዙሪያ በደሴ ከተማ ውይይት በተካሄደበት ወቅት በዩኒቨርሲቲው የዓሳና  የውሃ ሃብት ተመራማሪ  ዶክተር አሰፋ ተሰማ እንደገለጹት፤ ከአስር ዓመት በፊት በሃይቆቹ ውስጥ  ይገኝ የነበረው  የዓሳ  ስጋ ምርት   ከግማሽ በታች ወርዷል።

የዓሳ  ማጥመጃ መረቡ ስፋት  ስምንት  ሳንቲ ሜትር መሆን የነበረበት በህገ ወጥ አሳጋሪዎች  ከ5 ሳንቲ ሜትር በታች መሆኑ ለደረሰው ጉዳት አንዱ መንስኤ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሎጎ ሃይቅ የውሃ ስፋትና መጠንም ከ70 ዓመት በፊት ከነበረው ይዘት አሁን ላይ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው መቀነሱን በጥናት ማረጋገጣቸውን አመልክተዋል።

ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት  በሃይቆቹ ላይ የሚካሄደውን እንቅስቃሴ  ለሁለት ዓመት  በመገደብ የዓሳ ሃብቱን ቀድሞ ወደ ነበረበት በመመለስ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ  እንደሚቻል ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።

ለዚህም በዓሳ ማስገር የተሰማሩ ግለሰቦችንና ኑሯቸውን በሃይቁ ላይ የመሰረቱ የአካባቢው ነዋሪዎችን በሌሎች አማራጭ የስራ መስኮች ለማሰማራት ባለድርሻ አካላት  ድጋፍ ቢያደርጉ ሌላ የመፍትሄ ሃሳብ መሆኑን ዶክተር አሰፋ ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የሃይቆቹን ድንበር በመከለል፣ የተፈጥሮ ሃብት ስራ በመስራት፣ ውሃ በብዛት የሚጠቀሙ እንደ ጫት ያሉ ተክሎችን በቋሚ ፍራፍሬ በመቀየርና የሚለቀቁ ቆሻሻዎችን በማስወገድ በአጭር ጊዜ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይፉ ሰይድ በበኩላቸው በዞኑ ከሚገኙ አራት ሃይቆች ውሰጥ በስፋታቸውና በመጠናቸው ትልልቆቹ  የሎጎና አርዲፖ ሃይቆች ናቸው ብለዋል።

ሁለቱ ሀይቆች በቱሪዝም፣ ዓሳ ምርት፣ አትክልትና ፍራፍሬና ሌሎች የግብርና ምርቶች ለአካባቢው ህዝብ ጥቅም የሚሰጡ የተፈጥሮ ጸጋዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በህገ ወጥ የቤት ግንባታ፣ እርሻ መስፋፋት፣ ደለል፣ ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ በሀብቱ ላይ  የሚያደርሱት ችግሮችን ለማቃለል   በህግ ማስከበር ላይ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

 "እኛ እንደ ዞን አስተዳደር በምሁራን የሚቀርቡ ጥናቶችን መሰረት አድርገን ወደ ተግባር ለመግባት የተጀመሩ ሙከራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን" ብለዋል።

የአማራ ክልል የጣናና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር አያሌው ወንዴ እንዳሉት፤ የተከሰተውን ችግር ከክልል እስከ ቀበሌ ያለውን አካላት በማስተባበር ለመፍታት ተዘጋጅተዋል።

በቅርበት የሚገኙ ከተሞችና ወረዳዎች ከሚያመነጩት ሃብት ውስጥ ሃይቆቹን ለመጠበቅና ለመንከባከብ የሚውል በጀት እንዲይዙ በማድረግ በራስ አቅም ችግሮችን የመፍታት ዘዴን መከተል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ባለድርሻ አካላትም በእውቀትና ክህሎት ከማገዝ ባሻገር ተገቢውን ሃብት በመመደብ የምሁራኑን ጥናት መሰረት በማድረግ ሃይቆቹን ለመጠበቅና ለመንከባከብ  ማገዝ  እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ የሚገኙ የሚመለከታቸው  አካላት አስተሳስሮ በመምራት ሃይቆቹንና ብዝሃ ህይወቱን መታደግ የኤጀንሲው ዋና ተግባር እንደሚሆን አስታውቀዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር አፀደ ተፈራ ፤ ሃይቆቹ የተደቀነባቸውን ችግር ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በጥናቱ ውጤት ላይ ተመርኩዞ ለማልማትና ለመጠበቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና ግንዛቤ የመፍጠር  ስራ እየተከናወነ መሆኑን ቀደም ብለው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም