ተስፋ የጣሉባቸው ጉዳዮች እውን ሆነው ማየት እንደሚሹ የምርጫ ካርዳቸውን የወሰዱ ዜጎች ገለጹ

68

ሚያዚያ 6/2013 (ኢዜአ) ምርጫው ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተካሂዶ ተስፋ የጣሉባቸው ጉዳዮች እውን ሆነው ማየት እንደሚሹ በመራጭነት የተመዘገቡ አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ።

ምርጫው ሠላማዊ ሂደቱን ጠብቆ እንዲካሄድ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ሊካሄድ ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ ቀርቷል።

ሁሉም ዜጋ ምርጫው ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የዜግነት ሃላፊነት ተጥሎበታል።

በመሆኑም ዕድሜው ለመምረጥ የደረሰ ዜጋ አንድ ድምጽ ዋጋ እንዳለው በመረዳት የምርጫ ካርዱን በእጁ ማስገባት ይጠበቅበታል።

ኢዜአ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው የመራጭነት ካርድ የያዙ ሰዎች መጪው አገርአቀፍ ምርጫ ቀደም ሲል ከነበሩት የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት አላቸው።

አሁን በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ከምርጫው በኋላ መፍትሄ እንደሚያገኙም እንዲሁ።

የሠላምና የደህንነት ስጋቱ፤ የምጣኔ ሃብት ጫናውም ከምርጫው በኋላ ይቃለላል የሚል እምነት እንዳላቸው ነው የገለጹት።

የመራጥነት ካርድ የወሰዱት አቶ ፈይሳ ደጌቲ ባስተያየታቸው   "አንድነታችንን አጠናክረን ኢትዮጵያን ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ያደርሰናል ወደ ነበርንበት ይመልሰናል ስማችንን ያድስልናል የሚል ሀሳብ አለኝ።"

አስተያየት ሰጪዎቹ ምርጫው ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተካሂዶ ተስፋ የጣሉባቸው ጉዳዮች እውን እንዲሆኑም ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

"እየነቃ ያለ ወጣት ነው ልጆቻችንን ዛሬ እውነታውን ጥሩ ነገርን ነው ማስተማር ያለብን ነጻ ትውልድ እንዲፈጠርልን ልጆቻችን በነጻነት ይህቺን አገር እንዲረከቧት እንዲመሯት እኔም አሁን ካርዴን ዛሬ ቀድሜ የወሰድኩት የምፈልገውን የኔን ጥያቄ የሚመልስልኝን ፓርቲ ለመምረጥ ብዬ ነው" ያሉት የመራችነት ካርዳቸውን የወሰዱት አቶ እጅጉ ሃይሌ።

የምርጫ ካርድ ያልወሰዱ ዜጎች ካርዳቸውን በእጃቸው በማስገባት መብታቸውን እንዲጠቀሙ አስተያየት ሰጪዎቹ ጥሪ አስተላልፈዋል።

"እኔ ምርጫ ካርድ ወስጃለሁና ሂዱ ውሰዱ ምርጫ ካርድ ከወሰዳችሁ የፈለጋችሁትን ትመርጣላችሁ መብትም ታገኛላችሁ በመብታችሁ ትጠቀማላችሁ ብዬ አስተላልፋለሁ።" ያሉት ደጌሞ አቶ ሙስጠፋ አልቃድር።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቅ ዘጠኝ ቀናት ቀርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም