በጎንደር ከተማ ከ320 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማሻሻያ እየተሰራ ነው

53

ጎንደር  መጋቢት 30/201 (ኢዜአ) የጎንደር ከተማን የኤሌትሪክ አቅርቦት ለማሻሻል ከ320 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ አዳዲስ መስመሮችን የመዘርጋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

የጎንደር ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሞገስ አበራ ለኢዜአ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ የመብራት መቆራረጥን በማስቀረት ለከተማው አስተማማኝና በቂ የኤሌትሪክ ሃይል ለማቅረብ የሚያስችል ነው፡፡

“በፕሮጀክቱ በከተማው ከ50 አመታት በላይ ያገለገሉ የእንጨት ምሰሶዎች ወደ ኮንክሪት የሚቀየሩ ሲሆን ያረጁ መስመሮችና ትራንስፎርመሮችም ደረጃቸውን በጠበቁ ዘመናዊ የኤሌትሪክ ግብአቶች ይተካሉ” ብለዋል፡፡ 

የኤሌትሪክ መስመር ማሻሻያ ፕሮጀክቱ የከተማውን ማስተር ፕላን በጠበቀ መንገድ የሚከናወን ሲሆን 177 ኪሎ ሜትር መካከለኛ 77 ኪሎ ሜትር ደግሞ ዝቅተኛ መስመሮች በአዲስ የመቀየር ስራዎች ይከናወናሉ”ብለዋል።

በተጨማሪም ባለ 315፤ 200 እና 100 ኪሎ ቮልት አቅም ያላቸው 51 አዳዲስ ትራንስፎርመሮች ተከላ እንደሚከናወን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ 25 ያገለገሉ ትራንስፎርመሮችን አቅም የማሳደግ ስራ እንደሚካሄድም ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በአንድ የህንድ የኤሌትሪክ ኩባንያ የሚከናወን ሲሆን አራት የሀገር ውስጥ ተራጮችም በስራው ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ፕሮጀክቱ ባለፈው አመት ተጀምሮ በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ምክንያት ተቋርጦ መቆየቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ “ዘንድሮ ስራውን ዳግም በማስጀመር በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው” ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ከተመደበለት በጀት 200 ሚሊዮን ብር ያህሉ ከውጪ ሀገር በግዢ ለሚገቡ ትራንስፎርመሮችና የኤሌትሪክ መስመሮች የሚውል እንደሆነም አመልክተዋል።

ከ120 ሚሊዮን ብሩ የሚበልጠው ደግሞ ከሀገር ውስጥ ለሚገዙ የኮንክሪት ምሰሶዎች ወጪ የሚደረግ እንደሆነም ዳሬክተሩ አሰረድተዋል፡፡ 

የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ በበኩላቸው እንደተናገሩት አዲሱ የኤሌትሪክ ማሻሻያ ፕሮጀክት የከተማውን ህዝብ የረጅም አመታት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የሚፈታ ነው።

የከተማ አስተዳደሩ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ለኤሌትሪክ መስመሮች ዝርጋታ የሚውሉ ቦታዎችን ከሶስተኛ ወገን ነጻ በማድረግ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

“የከተማው የመብራት አገልግሎት ዝናብ በዘነበና ነፋስ በነፈሰ ቁጥር ለረጅም ሰአት የሚቆራረጥ ነው” ያሉት ደግሞ በከተማው የቀበሌ 4 ነዋሪ የሆኑት አቶ አስማረ ሲሳይ ናቸው፡፡ 

''በአካባቢያቸው በሃይል ማነስ ሳቢያ በኤሌትሪክ ምጣድ እንጀራ ለመጋገር አይቻልም'' ያሉት አቶ አስማረ “የመስመር ማሻሻል ስራው ችግሩን ያቃልልናል ብለን በተስፋ እየጠበቅን ነው” ብለዋል፡፡ 

በጎንደር ከተማ ከ40ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶችና ተቋማት የኤሌትሪክ ተጠቃሚ ደንበኞች መሆናቸውን ከዲስትሪክቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም