የዕደ ጥበብ ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው - የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር

152

ሐረር ፤ ሚያዚያ 05/2013(ኢዜአ) የዕደ ጥበብ እና ከዘርፉ የሚገኙ ውጤቶችን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

በሐረሪ ክልል የሚገኘውን የኢናይ አቢዳ የዕደ ጥበብ ማሰልጠኛ ኮሌጅ እና በዘርፉ ሙያ  የተሰማሩ ማህበራትን  የስራ እንቅሰቃሴ ተጎብኝቷል።

በሚኒስቴሩ የዕደ ጥበብ ማበልጸግና ገበያ ትስሰር ዳሬክቶሬት ባለሙያ ወይዘሮ ማስረሻ ኡርጌሳ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት፤  ዳይሬክቶሬቱ የእደ ጥበባት ውጤቶችን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ነው።  

በተለይ የዕደ ጥበባት ውጤቶች በጥናትና ምርምር ስራዎች እንዲታገዙ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰዋል።

ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር፣ከፋሽንና ዲዛይን ማህበራት እንዲሁም ከሌሎች ጋርም በገበያ ትስስር   ዘርፎች ላይ  እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በተለይ በየክልሉ የሚገኙ እና በዘርፉ የተሰማሩ ማሰልጠኛ ተቋማትና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ዘርፉን ወደ ተሻለ የእድገት ደረጃ እንዲደርስ በስልጠና እንዲያግዙ ፣ የብድር አገልግሎት እና የመስሪያ ቦታ እንዲመቻችላቸው ከባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ጋር እየሰሩ  እንደሚገኙም አስረድተዋል።

እንደ ባለሙያዋ ገለጻ፥ በዕደ ጥበብ ስራዎች ላይ በተለይ ስራ አጥ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በስልጠና ለማብቃት ጥረት እየተደረገ ነው፤ የሐረሪ ክልል ጉብኝት  ዓላማም በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን ለማበረታት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

በሐረር ከተማ የሚገኘው የኢናይ አቢዳ የዕደ ጥበባት ማሰልጠኛ ኮሌጅ ዲን አቶ ካሊድ አዋድ በበኩላቸው  ኮሌጁ ከተመሰረተ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በዓመት እስከ 400 ሰዎችን በመቀበል በእንጨት፣ ቆዳ፣ ስፌት ፣ጌጣጌጥ ፣ አልባሳት፣ሽመናና ሌሎች የዕደ ጥበባት ስራዎች ሙያ የማሰልጠንና የማብቃት ስራ እያከናወኑ  እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም በተለይ ሰልጣኝ ወጣቶች እና ሴቶች በማህበር ተደራጅተው በመንቀሳቀስ እራሳቸውን እየደገፉ እንደሚገኙ ጠቁመው ከዚህ አንጻር ዘርፉ ጎብኚዎችን  በመሳብ ረገድ   ከፍተኛ የቱሪስት መዳረሻ መሆን መቻሉን ተናግረዋል።

በኮሌጁ የሚሰጠው ስልጠና የዕደ ጥበባት እንዳይጠፉና ወጣቱ ትውልድ ደግሞ ተንከባክቦ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላልፍ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ያሉት ደግሞ የኮሌጁ  አሰልጣኝ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዶሽ ናቸው።

በተለይ በአሁኑ ወቅት በኮሌጁ ከሐረሪ ሌላ  የተለያዩ የአካባቢው ተወላጆች መጥተው በመሰልጠን የራሳቸውን ስራ ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል።

በኮሌጁ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ሰልጥነው  በመደራጀት ወደ ስራ የተሰማሩት ወይዘሮ መዲ አብዱልዋሲ በሰጡት አስተያየት፤ ከኮሌጁ ባገኘችው የስድስት ወራት ስልጠና ተደራጅተው ወደ ስራ በመግባት  ገቢ እያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከኮሮና ጋር  በተያያዘ የቱሪስት ፍሰቱ በመቀዛቀዙ የገበያ እጥረት ቢኖርባቸውም በዓላትንና ሌሎች አጋጣሚዎችን በመጠቀም እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም