መንግስት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ እድገት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል- የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

134

ደብረብርሃን ፤ ሚያዚያ 05/ 2013(ኢዜአ) መንግስት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍን ለማሳደግ አደረጃጀትና አሰራር በመዘርጋት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

የደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ  የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሳምንት በዓልን  ምክንያት በማድረግ በዘርፉ ምርምሮች ላይ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

በምክክር መድረኩ የተገኙት በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር  የሳይንስ ባህል ግንባታ ዳይሬክተር ዶክተር ዱላ ቶሌራ እንደገለጹት፤ ወጣቱን በሳይንስ ባህል ግንባታ በማነጽ በእውቀትና ክህሎት ተወዳዳሪ እንዲሆን ማዘጋጀት  ያስፈልጋል።

ለዚህም መንግስት ከሚኒስቴሩ  ጀምሮ እስከ ታች ድረስ አደረጃጀትና አሰራር በመዘርጋት ለዘርፉ እድገት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ  መሆኑን ተናግረዋል።  

ከታች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ያሉ ተማሪዎች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ላይ በማተኮር እውቀትና ክህሎታቸውን ማዳበር የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል።

ከ30 በላይ በሚሆኑ ዩኒቨርስቲዎች የሳይንስና ቋንቋ ትምህርት  ማዕከላት ተደራጅተው ስራ በመጀመራቸው የቀጣዩ እድገታችን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ እንዲመሰረት የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፊዚክስ፣ ኬሚስትሪና ሌሎች የሳይንስ ዘርፎች ላይ የሚካሄዱ ጥናትና ምርምሮች እያደጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ይህም ወጣቱ ትውልድ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ባህልን በማድረግ ዘላቂነት ያለው የሀገር ብልጽግናን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።

በደብረ ብርሀን ዩኒቨርስቲ የጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚደንት ዶክተር አዝመራ አየሁ በበኩላቸው፤ ለሳይንስ ባህል ግንባታ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የሳይንስ ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን እውቀትና ክህሎት ሁለንተናዊና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ከማረጋገጥ ባሻገር ሀገራት ዓለም ላይ ያላቸውን የተጽዕኖ ፈጣሪነት ለማሳደግ ተመራጭ ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከስምንት ዓመታት በፊት በዘርፉ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማምጣት ቴክኖሎጂን በመቅዳት፣ በማላመድና ስራ ላይ በማዋል ውጤቶች ቢኖራትም በሚጠበቀው ደረጃ አለማደጉን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲውም መንግስት ያስቀመጠውን አቅጣጫ መሰረት በማድረግ የኢኖቬሽንና ቴክኖለጅ ሽግግር ዳይሬክቶሬት በማቋቋምና የምርምር ማዕከላትን በማደራጀት ወደ ስራ መግባቱን አውስተዋል።

ከአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በፈጠራ ስራቸውና በቀለም ትምህርት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ከ100በላይ ተማሪዎችን ቅዳሜና እሁድ በስድስት የትምህርት ዓይነቶች የተግባር ስልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሳምንት በዓል ምክንያት በማድረግ ለአራት ቀናት በተዘጋጀው  መድረክ  የዘርፉ እድገት ለማፋጠን  የሚያግዙ ምርምሮች ቀርበው ውይይት የሚካሄድባቸው ሲሆን ከአዲስ አበባና ከአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የመጡ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የፈጠራ ስራዎቻቸውን ቀደም ብለው አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም