ሱዳንና ግብፅ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚያሰሙት የጦርነት ነጋሪት ማቆም አለባቸው ሲል ዘስታንዳርድ ጋዜጣ ገለጸ

107

ሚያዚያ 5 /2013 (ኢዜአ) ዘ ስታንዳርድ የተሰኘው የኬንያ ጋዜጣ በርእሰ አንቀጹ ባስነበበው ዘገባ ሱዳንና ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሉትን አለመግባባቶች ለመፍታት የጦርነት ነጋሪት ከመምታት እንዲያቆሙና ጉዳዩን በውይይትና በድርድር እንዲፈታ ማድረግ አለባቸው ሲል ገልጿል።

ሶስቱም ሃገራት ለህዝቦቻቸው ተጠቃሚነት መትጋታቸው የሚጠበቅ ቢሆንም ወንዙ የ11 የተፋሰሱ ሃገራት የጋራ ንብረት መሆኑ ሊዘነጋ እንደማይገባ ያስታወሰው፤ ርእሰአንቀጹ በቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ላይ ተመስርቶ ሱዳንና ግብጽ የደረሱበት የውሃ ክፍፍል ስምምነት የተፋሰሱን ሃገራት የጋራ ተጠቃሚነት ስለሚያስቀር ኢትዮጵያ ስትቃወመው እንደነበር አስታውሷል።

ሁሉም የወንዙ ተጋሪ ሃገራት ውሃውን በሃላፊነት መንፈስ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ መግባባት ላይ መደረስ እንዳለበት ያተተው ጋዜጣው፤ ግብጽና ሱዳን ወንዙ የእነርሱ ብቻ እንደሆነ አድርገው የሚያራምዱትን አቋም ማስተካከልና በተፋሰሱ ሃገራት ውስጥ አለመረጋጋት ለመፍጠር ከመስራት መቆጠብ እንዳለባቸው ገልጿል።

በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኪንሻሳ ሲካሄድ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር ባለመስማማት መጠናቀቁን ተከትሎ የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ “አንዲት ጠብታ ውሃ ብትነካ የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ወደ አለመረጋጋት ይገባል” ሲሉ መናገራቸውን አስታውሶ፤ ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው የኤሌክትሪክ ሃይል በማመመንጨት ለመጠቀምና ለጎረቤት ሃገራትም ለማካፈል መሆኑን አስነብቧል።

ርእሰ አንቀጹ ሶስቱም ሃገራት ከመራራቅ ይልቅ ተቀራርበው በመነጋገር ኢትዮጵያ ግድቡን ሌሎችን በማይጎዳ መልክ እንድትሞላ ሊያደርጉ እንደሚገባ የመከረ ሲሆን የኪንሻሳው ድርድር አለመሳካት የሁሉ ነገር መጨረሻ ባለመሆኑ ተከታታይ ንግግሮች ሊደረጉ እንደሚገባም መክሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም