በዘንደሮው ምርጫ የማህበረሰቡ ተሳትፎ በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ለማስቻል ምሁራን የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

70

ማያዚያ 4/2013 (ኢዜአ) በዘንደሮው ምርጫ የማህበረሰቡ ተሳትፎ በእውቀትና በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ለማስቻል ምሁራን የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ፡፡

“በሀገሪቱ የፖለቲካና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት የምሁራን፣ የፖለቲካ ሊህቃን እና የመራጮች ሚና” በሚል መሪ ሃሳብ የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠት ተጀምሯል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደርና መሰረተ ልማት ጉዳዩች ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን አብርሃም ስልጠናው ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የምሁራንን ተሳትፎና እገዛ ለማጠናከር መሆኑን ገልጸዋል

ከምርጫ በፊትም ሆነ በኋላ በሚኖሩ ሒደቶች ላይ በግልጽ ውይይት በማድረግና ማብህረሰቡን በማንቃት ምሁራኑ የጎላ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማስቻል መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ምሁራኑ የማህበረሰቡ ተሳትፎ በእውቀትና በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ለማስቻል የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ምሁራን እና የፖለቲካ ሊህቃን በተለይ የምርጫ ተወዳዳሪዎችን እና መራጮችን በማንቃት ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ፣ፍትሃዊ እና አሳታፊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መስራት አለባቸው ተብሏል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩር አማካሪ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ባደረጉት ንግግር ምሁራን እና የፖለቲካ ሊህቃን የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በማጤን ምሁራዊ ምልከታቸውን ማጋራት አለባቸው ብለዋል።

ሌሎች አገሮች ከምርጫ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ እንዲሁም ያጋጠሟቸውን ችግሮች በመተንተን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ቢችሉም በእጂጉ ጠቃሚ መሆኑን አንስተየዋል።

የውይይት መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት ዶክተር ዮናስ በቀለ እንዳሉትም ምሁራኑ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ በመተንተንና ሕብረተሰቡን በማንቃት ዙሪያ እብዛም ተሳትፎ ሲያደርጉ አይስተዋልም።

በመሆኑም በዘንድሮው ምርጫ ዜጎች ይወክለኛል ያሉትን ፓርቲ በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መምረጥ አንዲችሉ የምሁራኑ ሚና ላቅ ያለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ምሁራን የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

በስልጠናው ላይ ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ክላስተሮች የተውጣጡ ምሁራን ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም