በአሶሳ የሃይማኖት አባቶች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ ክትባት ወሰዱ

70

አሶሳ ፤ ሚያዚያ 04 / 2013(ኢዜአ) በአሶሳ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ ሃይማኖት አባቶች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ ክትባት ወሰዱ፡፡

የሃይማት አባቶቹ  ክትባቱን የወሰዱት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ዛሬ በአሶሳ ከተማ በተዘጋጀ የቅስቀሳ መድረክ ላይ ተገኝተው ነው፡፡

ክትባቱን ከወሰዱት መካከከል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአሶሳ ሃገረ ስብከት ማደራጃ መምሪያ ሃላፊ ሊቀ-ብርሃናት ቀሲስ ፍቅር ሰጠኝ እንዳሉት፤ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሃይማኖት አባቶች ተሰሚነታውን ተጠቅመው የድርሻቸውን ካልተወጡ መንግስት ብቻውን የሚፈለገውን ለውጥ አያመጣም፡፡

ክትባቱን በተመለከተ የሚነሱ  አሉባልታዎች መኖራቸውን የገለጹት ሃላፊው  የቫይረሱ መከላከያ  ክትባት ላይ ጥርጣሬ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

መንግስት ህዝቡን የሚጎዳ ህክምና ሆነ የትኛውምን ነገር ወደ ሃገር አስገብቶ ለዜጎች አይሰጥም ብለዋል፡፡

የጥበብ ባለቤት እግዚአብሄር ነው ያሉት ሊቀብርሃናት ቀሲስ ፍቅር መድሃኒቱን በምርምር ላገኙ እና ላቀረቡ የሀገሪቱ መንግስታዊ ተቋማት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በአሶሳ ከተማ የአንዋር መስጊድ ምክትል አስተዳዳሪ ሼክ አብዱ ሃሰን በበኩላቸው የሃይማኖት አባቶች የኮሮናን ስርጭት ለማስቆም ምዕመናንን ተግተው ማስተማር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ክትባቱን ደግሞ በመንፈሳዊ አገልግሎት በሚፈጠር ግንኙነት ከቫይረሱ ራሳቸው ጠብቀው ሃላፊነታውን በበለጠ እንዲወጡ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡

ክትባቱን በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ ያሉት ደግሞ በአሶሳ የምስራች ወንጌል ቤተክርስቲያን መሪ ሃዋርያ ክፍሌ ይልማ ናቸው፡፡

ኮሮና በሃገሪቱ የዜጎችን ህይወት እየነጠቀ ቢሆንም የህብረተሰቡ መዘናጋት ቀጥሏል ያሉት የሃይማኖት መሪው ይህ ደግሞ በሃይማኖት ተቋማት ጭምር እንደሚታይ አመልክተዋል፡፡

ከመቼውም በላይ ህብረተሰቡን ማስማር ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል  ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ፈዋዱ ረጋሳ  በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በፍጥነት መጨመሩን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በየቀኑ ከሚመረመሩት ሰዎች ውስጥ እስከ 40 በመቶ ቫይረሱ ይገኝባቸዋል፤ ወደ ጽኑ ህክምና የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል ብለዋል፡፡

ባለፈው አንድ ወር የ11 ሰዎች ህይት ማለፉን ጠቁመው ወደ ጤና ተቋማት ሳይመጡ ህይወታቸው የሚያልፉም እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ከመጋቢት 25 / 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት የቫይረሱን መከላከያ መመሪያዎችን አስገዳጅ ለማድረግ ጥረት ተጀምሯል ብለዋል፡፡

 ይሁንና በመንግስት ተቋማት ያለጭንብል   አገልግሎት ባይሰጥም በህብረተሰቡ ዘንድ  መዘናጋቱ መቀጠሉን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም