የአፍሪካ የፖሊስ ተቋማትን ለማሳደግ ልምዶችና እውቀቶችን መለዋወጥ ያሥፈልጋል – የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

654

ሚያዚያ 4 / 2013 (ኢዜአ) የአፍሪካን የፖሊስ ተቋማትን በሁሉም ረገድ ለማሳደግ የእርስ በእርስ ልምዶችና እውቀቶችን መለዋወጥ እንደሚያስፈልግ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡

ለምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል አባል አገራት ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች በሠላም ማስከበር ቅድመ ስምሪት ዙሪያ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

ሰንዳፋ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ በሚሰጠው ስልጠና ከኢትዮጵያ፣ ከዩጋንዳ፣ ከኮሞሮስ፣ ከጅቡቲ፣ ከሶማሊያ፣ ከኬኒያና ብሩንዲ የተወጣጡ የፖሊስ መኮንኖች ተሣታፊ ሆነዋል።

ኮሚሽነር ጄኔራሉ በስልጠናው መጀመሪያ አፍሪካዊያን እርስ በርስ በመተጋገዝ የፖሊስ ተቋሞቻቸውን ጠንካራ ማድረግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

በአፍሪካ ጠንካራ የፖሊስ ተቋም መፍጠር ካልተቻለ የተለያዩ ግጭቶች አፍሪካዊያን ወንድማማቾችን ወደ እርስ በእርስ ጦርነት የመውሰድ እድላቸው ሰፊ መሆኑን አንስተዋል።

አፍሪካዊያን ሠላማቸውን በማስጠበቅ ያላቸውን ሃብት ለልማት ማዋል እንዳለባቸውም ጨምረው ገልጸዋል።

ይህን በማድረግ የፓን አፍሪካኒዝምን ህልም ማሳካት እንደሚቻልም አስረድተዋል።

ኮሚሽነር ጄኔራሉ አክለውም፤ ኢትዮጵያ ስልጠናውን ለማዘጋጀት በመመረጧ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ሰልጣኞች በቆይታቸው ለስራቸው የሚያስፈልጋቸውን እውቀትና ክህሎት እንደሚያዳብሩም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ዳይሬክተር ብርጋዴል ጄኔራል ጌታቸው ሽፈራው በበኩላቸው ስልጠናው ወደ ሠላም ማስከበር የሚሄዱ የፖሊስ አባላት ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲፈጽሙ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ይህም ለቀጣናው የጋራ ሠላም፣ ዕድገትና ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ስልጠናውን ማዘጋጀቱ ዓለም አቀፍ ልምዶችና ተሞክሮዎችን እንዲያገኝ እንደሚያስችለው የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መስፍን አበበ ናቸው። 

ስልጠናውም ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፤ በስልጠናው 47 የፖሊስ መኮንኖች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ከዚህም ውስጥ 20ዎቹ ኢትዮጵያን የወከሉ ሲሆኑ 27 የፖሊስ መኮንኖች ደግሞ ከተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ አገራት የመጡ ናቸው።

የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል 10 አባል አገራትን የያዘ ነው።