የቴክኖሎጂ ልማት ሽግግርን በማረጋገጥ የሥራ አጥነት ችግሮችን ለመፍታት እየሰሩ መሆናቸውን የዘርፉ አምራቾች ገለጹ

1833

ባህርዳር፤ሚያዚያ 4/2013(ኢዜአ) የቴክኖሎጂ ልማት ሽግግርን በማረጋገጥ የአርሶ አደሩንና የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ ስራዎች እያካሄዱ መሆናቸውን በአማራ ክልል በቴክኖሎጅ ልማት የተሰማሩ አምራቾች ገለጹ።

ሰባተኛው ክልል አቀፍ የቴክኖሎጂ፣ ክህሎት፣ የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድርና ሲምፖዚየም በደሴ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በዝግጅቱ እየተሳተፉ ካሉት መካከል የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ አቶ ባንታለም አየሁ እንዳሉት ዘመናዊ የበቆሎ መፈልፈያና የጤፍ መውቂያ ማሽኖችን በማምረት የአርሶ አደሩን የዘመናት ችግር ለመፍታት እየሰሩ ነው።

እስካሁንም ስድስት የበቆሎ መፈልፈያና ሶስት የጤፍ መውቂያ ማሽኖችን በማምረት ለተደራጁ ወጣቶች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ እንዲጠቀሙ ማገዛቸውን ገልጸዋል።

የበቆሎ ማሽኑ በሰዓት 40 ኩንታል በቆሎ መፈልፈል የሚያስችል መሆኑ በተግባር ተረጋግጧል ብለዋል።

በቀላሉ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቃሽ መሆናቸው፣ በአነስተኛ የሀይል ማምንጫ ጀነሬተርና ነዳጅ መስራታቸው ማሽኖቹ በወጣቶቹ  ተመራጭ ያደርጋቸው መሆኑን አስረድተዋል።

በዋጋ አንጻርም ከህንድ የሚመጣ አንድ የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን ከ200ሺህ ብር በላይ የሚጠይቀው እሳቸው የሚያመርቱት በ60ሺህ ብር እንደሚሸጥም ተናግረዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ የመቅድም ሁለገብ ማሽነሪዎች ማምረቻ ድርጅት ባለቤት አቶ መቅደም ሃይሉ በበኩላቸው በዝግጅት ያመረቱት ባለ ሶስት እግር ባጃጅ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

በኤሌክትሪክ ሃይል የምትሰራው ባጃጇ ቻርጅ በማድረግ 40 ኪሎ ሜትር የምትጓዝ ከመሆኑም በላይ ጎማዋን ከፍ በማድረግ አደጋን በመከላከል ለተገልጋዮች ምቹ መሆኗን ጠቅሰዋል።

ለባጀጅ የሚሆን በኤሌክትሪክ የሚሰራ ሞተር፣ የፍጥነት መቆጣጠሪያና ቻርጀሩ ከውጭ እንደሚገባ ገልጸው ሌላው የባጃጅ ክፍል በሀገር ውስጥ ቁሳቁስ የተሰራች፣ የነዳጅ ወጪና የአየር ብክለትን በመቀነስ ለአካባቢ ተስማሚ ነች ብለዋል።

አሁን አብረዋቸው የሚሰሩ ሁለት ወጣቶች እንዳሉ ጠቁመው በቀጣይ የመካኒካል፣ የኤሌክትሪክና የአውቶሞቲቭ ምሩቃንን በመቅጠር በዓመት 20 ባጃጆችን በማምረት ለገበያ ለማቅረብ ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

“ለአንድ ሃገር እድገት ዋናው መሰረት የአምራች ኢንዱስትሪው ተጠናክሮ ከውጭ የሚመጣ ምርትን በሀገር ውስጥ መተካት ሲቻል ነው” ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት እስሌማን ኢብራሂም ናቸው። 

የፈጠራ ሰዎችንና አምራቾችን በቴክኒክና ሙያ ተቋማት በማገዝ በብዛትና ዓይነት በስፋት ማምረት አማራጭ እንደሌለው ጠቁመው በዚህም የምክር ቤቱ አባላት የሚያጋጥሟቸውን ክፍተቶች ለመሙላት በየደረጃው ከሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጋር ተባብረው ለመስራት ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።

የአማራ ክልል ቴክኒክ፣ ሙያና ኢንተርፕራይዞች ቢሮ ሃላፊ አቶ አረጋ ከበደ እንዳሉት፤ ሀገሪቱ ባላት አቅም የቴክኖሎጂ ልማትና ምርምርን ለማስፋፋት የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀትና አሰራር ፈጥራ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች።

የቴክኖሎጂ ልማት የሰው ልጅ የአኗኗር ዘይቤ እንዲሻሻልና የችግሮች ሁሉ ማምለጫ መንገድ በመሆኑ በክልሉ ቴክኖሎጂን መኮረጅ፣ ማላመድ፣ በስፋት ማምረትና ማሰራጨት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በደሴ ከተማ እየተካሄደ ያለው ዝግጅትም የቴክኖሎጂ አቅምና የመወዳደር ብቃት የሚገመገምበት፣ በዘርፉ የተማሩ ተዋናዮች ተነሳሽነት የሚያድግበትና የገበያ ትስስር የሚፈጥርበት መሆኑን አስረድተዋል።

በፌደራል ደረጃ ለሚካሄደው ሀገር አቀፍ የቴክኖሎጂና የተግባር ተኮር ምርምር ውድድር ብቁ ተወዳዳሪ ከመሆን ባሻገር በሁሉም ዘርፎች አሸናፊ ለመሆን የምንዘጋጅበት መሆን አለበትም ብለዋል።

በአማራ ክልል ከሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና የግል አንቀሳቃሾች በ18 የሙያ መስኮች ተወዳድረው የሚያሸንፉ አሰልጣኞች፣ ሰልጣኞች፣ አንቀሳቃሾች ሚያዚያ 13 /2013 ዓ.ም በሚጀመረው የፌደራል ውድድር እንደሚሳተፉ ተመልክቷል።

በደሴ ከተማ ለአምስት ቀናት የተዘጋጀው ሰባተኛው ክልል አቀፍ የቴክኖሎጂ፣ ክህሎት፣ የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድርና ሲምፖዚየም ከሁለት ቀናት በኋላ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።