ከካርቦን ንግድ ሽያጭ ከ149 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱ ተገለጸ

221

ጎባ ሚያዝያ 3/2013 /ኢዜአ/ በባሌና ምዕራብ አርሲ ጥብቅ ደኖች ሲተገበር በቆየው የበካይ ጋዞች ቅነሳና የደን ጭፍጨፋን የመቀነስ ፕሮጀክት (ሬድ ፕላስ) አማካይነት በተሸጠው የካርቦን ንግድ ከ149 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱ ተገለጸ፡፡

በካርቦን ንግድ ሽያጩ የተገኘውን ውጤት በተፈጥሮ ኃብት ልማት ለተሰማሩ ማህበራትና ሌሎች ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ይፋ የማድረጊያ ውይይት ትናንት በባሌ ሮቤ ተካሄዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ልማት ኢንተርፕራይዝ ዋና ዳሬክተር አቶ አራርሳ ረጋሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢንተፕራይዙ ዘላቂ የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃና የህዝቡ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡

ባለፉት አስር ዓመታት በሁለቱ የባሌና ምዕራብ አርሲ ዞኖች በሚገኙ ጥብቅ ደኖች ውስጥ በሬድ ፕላስ ፕሮጄክት አማካይነት በተተገበረው የተፈጥሮ ኃብት ልማትና ጥበቃ የተገኘው አመርቂ ውጤትን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡

ፕሮጄክቱ በመተግበሩ ጉዳት ይደርስበት የነበረው 12 ሺህ 500 ሔክታር የሚሸፍን የደን ሀብትን በመጠበቅ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የካርቦን ጋዝ ልቀትን በማስቀረት ከ149 ሚሊዮን ብር በላይ ከከርቦን ሽያጭ ገቢ ማግኘት መቻሉን አቶ አራርሳ አስረድተዋል፡፡

ከተገኘው ገቢ ውስጥም 40 በመቶ የሚሆነው በኢንተርፕራይዙ በኩል ለዘላቂ የደን ልማትና ጥበቃ የሚውል ሲሆን 60 በመቶ የሚሆነው 36 ለሚሆኑ ለተፈጥሮ ኃብት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ድርሻ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡


የምሥራቅ ባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደም ቃሲም በበኩላቸው መንግስት ዘላቂ የተፈጥሮ ኃብት ልማትና ጥበቃ እንዲረጋገጥ አዳዲስ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ የተፈጥሮ ደን ሽፋንን ለመጨመር ለተፋሰስ ልማት ስራዎችና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብት ፕሮግራሞች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡

ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተሰራው ስራ ከፕሮጄክቱ ውጤት በመገኘቱ ለተሳታፊ ማህበራት ብቻ ሳይሆን ህዝብን ለሚያስተዳድሩ አካላትም ትልቅ እፎይታ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ደን መንከባከብና መጠበቅ የካርቦን ሽያጭን ለማካሔድ ከማስቻሉም በላይ ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ያብራሩት ደግሞ በፋርም አፍሪካ የሬድ ፕላስ ኢትዮጵያ የኦሮሚያ ክልል ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ኑራ አማን ናቸው፡፡


በፕሮጄክቱ እ.ኤ.አ. ከ2012 እስከ 2015 በነበረው የመጀመሪያ ዙር ጊዜ ውስጥ በተደረገ ክትትል ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ሲተገበር ከቆየው የበካይ ጋዞች ቅነሳና የደን ጭፍጨፋን የመቀነስ ፕሮጀክት  የደን ምንጣሮ መጠንን በ62 በመቶ ለመቀነስ ተችሏል ብለዋል፡፡

ከ2016 እስከ 2019 በተደረገው የሁለተኛው ዙር ትግበራ ደግሞ 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ካርቦን ለሽያጭ ለማቅረብ በዓለም አቅፍ አማካሪዎች በማስጠናት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

"የተፈጥሮ ኃብትን የምንከባከበው ለካርቦን ሽያጭ ብቻ ብለን ሳይሆን ለዘላቂ ህይወታችን መቃናት ነው" ያሉት ደግሞ በሀረና ወረዳ ቢርቢርሳ የተፈጥሮ ሀብት ማህበር አስተባባሪ አቶ አልይ ጅሎ ናቸው፡፡

በፕሮጄክቱ ተሳትፎ የደረሳቸው የ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ድርሻ ለተፈጥሮ ኃብት እንክብካቤ የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንደሚጨምርም አመልክተዋል፡፡

በሽያጩ ያገኙትን ድርሻ የማህበሩን ቋሚና ዘላቂ ገቢ በሚያስገኙ የኢንቨስትምንት አማራጮች ላይ እንደሚያውሉት የማህበራት ተወካዮቹ አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በፓርላማ ሕግ ሆኖ ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ እንዲሁም የሬድ ፕላስ ፕሮጀክት ላለፉት ዓመታት በተፈጥሮ ኃብት ልማትና ጥበቃ መስክ ባከናወናቸው ተግባራት አመርቂና ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን ከመድረኩ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም