የእሳት እራት

175

በአየለ ያረጋል--/ኢዜአ/

ከሰማይና ምድር በኋላ ሕይወታዊያን ፍጡራን (ሰውና ተክል) ተፈጥረዋል። የዕጽዋት ብዝሃ ሕይዎት ደግሞ ደንን መስርቷል። ሰውና ደን በቁርኝት ሲኖሩ ሰው ሕይወቱን አሻሽሎ ለመምራት እሳትን በምርምር ፈጥሯል። ደንና እሳትም የእሳት ቴክኖሎጂ ከተፈጠረ ጀምሮ የጥፋትም፣ የልማትም መስትጋብር ይዘው እልፍ ዘመናትን ተሻግረው ዛሬ ደርሰዋል። በተለይም የአየር ንብረት መዛባት ቀውሷ ለበዛባት ምደር ዛፎች የሕልውና መሰረት ናቸው። የዓለማችን ሳንባዎች ጥቅጥቅ ደኖች መሆናቸው እሙን ነው።

በኢትዮጵያ በአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪው ዶክተር ምናሴ ጋሻው ደንና እሳትን በሶስት መንገዶች ያቆራኙታል። አንድም የሰው ልጅ እሳትን ከፈጠረበት አንስቶ ደንና እሳት የተገናኙበትና እሳትን ለምዶ፣ ቃጠሎን ተቋቁሞ የሚኖር ደን ነው። በዚህ ምድብ የሚመደቡ ደኖች ዘራቸውን የሚተኩት እንኳ በእሳት ምክንያት ፍሬያቸውን በመበተን በመሆኑ እሳት ሕልውናቸው መሰረት ነው። ሁለተኛው እሳትን የማያውቅ ደን ሲሆን እሳት ቢያገኘው ድምጥማጡ የሚጠፋ ደን ነው። ሶስተኛው ደግሞ በከፊል እሳታዊ የሆነ ማለትም ብዙም እሳት የማይጎበኘው አንዳንዴ እሳት የሚሰደድበት ደን ነው። ይህም በተወሰኑ እሳትን ተቋቋሚ፣ ቀሪዎች ደግሞ የሠደድ እሳት ራት የሚሆኑበት ደን አይነት ነው።

እሳት በደረቅ የአየር ሁኔታ፣ ለእርሻ፣ ለኑሮ ግልጋሎት አልያም በእንዝላልነት ይነሳል። በኢትዮጵያ በወርሃ ሐጋይ በተለይም ከጥር እስከ ሚያዚያ በደረቀማና ነፋሻማ አየር ሁኔታ ይከሰታል። ማሳን ለማጸዳት፣ ሲጋራ ለማጨስ፣ የጫካ ማር ለመቁረጥ… እሳትን ይለኩሳሉ፣ ግን በንዝላልነት ካልጠፋ ለሌላ አገልግሎት የተለኮሰ እሳት ለደኖች ሠደድ ይሆናል። የደን ሠደድ እሳት ደኖችን ብቻ ሳይሆን ሕይወትን ያሳድዳል። የዜጎቿ ከ80 በመቶ ያላነሰው አርሶ አደር በሆነባት ኢትየጵያ በህዝብ ቁጥር ማሻቀብና የመሬት ፍላጎት መናር ደኖች በእሳት እንዲያያዙ እያደረገ መጥቷል። በሌሎች ዓለማትም ያደረጉ አገራትን ጨምሮ ‘ሰደድ እሳት’ ለዓለም ሳንባ በሆኑ ደኖች ላይ ‘የእግር እሳት’ ሆኗል።


ግጭት ለደን ሠደድ እሳት እንደ መንስኤ

ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ ካላት አየር ንብረት አኳያ ከፍተኛ የደን ሽፋን እንደነበራት መገመት አያዳግትም። የደን ተመራማሪዎቹም ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት 40 በመቶ በላይ ገላዋ በደን የተሸፈነ እንደነበር ጽፈዋል። ዛሬ የደን ሽፋኗ ተመናምኗል። ለዚህም መንስኤ አንዱ በጥንት ታሪኳ ጀምሮ ደኖቿ የእሳት ራት እየሆኑ መምጣታቸው ነው።

ታሪክ እንደሚነግረን ከ1 ሺህ ዓመት ገዳማ ዮዲት ጉዲት (የአክሱምን ስርዎ መንግስትን የገለበጠች ንግስት) ጠላቷን አጼ ድልናወድን መሰወሪያ ስፍራ ለማሳጣት ከአክሱም ጀምሮ እስከ ጎንደርና ወሎ ያለውን ስፍራ አገር በእሳት አቃጥላለች። በ16ኛው ክፍለ ዘመን ከምስራቅ ኢትዮጵያ የተነሳው ግራኝ አህመድ ባደረገው ወረራ የወቅቱን ተሳዳጅ ንጉሠ ነገሥት አጼ ልብነ ድንግልና ሰራዊቱን መደበቂያ ለማሳጣት ከምስራቅ ኢትዮጵያ ቆላማ አካበቢዎች እስከ ደጋማው የኢትዮጵያ ክፍል ያለውን የኢትዮጵያ ገላ በሠደድ እሳት እንዲቃጠል አድረጓል። እነዚህ ክስተቶች ኢትዮጵያ ከጥንትም በሰደድ እሳት ገለዋ ስለመጠበሱ በቂ ማስረጃዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ በጦርነት ገላዋ ተጠብሷል። በእርስ በርስ ግጭት ዛሬም የንጹሃን ዜጎች ህይወት ያልፋል ይሳደዳሉ፣ ይፈናቀላሉም። የሰዎች ግጭት ግን ከሰዎች አልፎ በተፈጥሮ ሃብቶች ላይ ውድመትንም አስከትሏል። በኢትዮጵየ በተለያዩ ወቅቶች እርስ በርስ ጦርነቶች ማለትም የጎሳና የፖለቲካ ወለድ ግጭቶች ምክንያት ደኖች የሳት እራት ሆነዋል ይላሉ ዶክተር ምናሴ። ከእርሻ፣ ከኢንቨስትመንት፣ ከሰል ማክሰል ወይም ከሌላ ጥቅም ባሻገር በግድየለሽነት ብቻ ብሔራዊ ፓርኮችን ጨምሮ በርካታ ደኖች ላለፉት 5 ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት ሲደርስባቸው እንደነበር ያነሳሉ።

ዶክተር ምናሴ ከሁለት ዐስርት ዓመታት በፊት በተደረገ ጥናት በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ250 ሺህ እስከ 300 ሺህ ሄክታር ደን በሠደድ እሳት ሳቢያ ታጣለች። አንድ ዛፍ ማጣት ከፍተኛ ጉዳት አለው የሚሉት ዶክተር ምናሴ፣ በ100 የጣውላ ዛፎች ብታጣ እንኳ በዓመት እስከ 5 ሚሊዮን ምጣኔ ሃብታዊ ኪሳራ እንደሚደርስባትና ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን ያስረዳሉ። በሰው ሰራሽ ኩርፊያ የተፈጥሮን ደን ማውደም አሳዛኝ ድርጊት ነው። ሽፍታ ወይም የደፈጣ ተዋጊዎችን መደበቂያ ለማሳጣትም ደኖች ለቃጠሎ ይደረጋሉ። ሽፍታን ለማሳደድ ደኖች በሰደድ እሳት ይሳደዳሉ። በጦርነት ወቅት፣ በፖለቲካና መሰል ግጭቶች ደኖች ይወድማሉ።

የዱር ሠደድ እሳት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ "አቅመ ቢስ" አገራት ቀርቶ የመከላከያ ቴክኖሎጂ ባላቸው በሌሎች አገራትም (አሜሪካና አውስትራሊያን ልብ ይሏል) ለመቆጣጠር ከባድ ነው። ሰደድ ምድር ለምድር፣ ቋጥኝ ለቋጥኝ፣ ሳር ለሳር… ተቀጣጣይ ነገሮችን በሙሉ እያያያዘ ይንቀለቀላል። የእንስሳት፣ አዕዋፋትና ሰዎችም ሕልውና ያናጋል።

በኢትዮጵያ ሌላው የሚከሰተው ሠደድ እሳት ይባስ ብሎ የብርቅዬ ብዝሃ ሕይወት ማዕከልና የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ ብሔራዊ ፓርኮችን ሰለባ ማድረጉ ነው። ይህም መዘዙ ድርብ ድርብርብ ነው። በየዓመቱ ፓርኮች ይወድማሉ፤ በዚህ ዓመት እንኳ በርካታ ብሔራዊ ፓርኮች በከፍተኛ ደረጃ ወድመዋል። ስሜን ብሔራዊ ፓርክ፣ ባሌ፣ የሃላይደጌ አሰቦት፣ የወፍ ዋሻ፣ ጭላሎ ተራራን ማንሳት ይቻላል። በቅርብ ዓመታት ውስጥም ስሜን ተራሮችና የቃፍታ ሽራሮ ፓርክች በከፍተኛ ደረጃ መቃጠላቸው አይዘነጋም። የኢትዮጵያ ዱር እንሳት ጥበቃ ባለስልጣን በቅርቡ በሰጠው መግለጫም ፓርክች በዚህ ዓመት ለተከሰቱ የሰደድ አሳት መንስኤዎች አብዛኞቹ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በሰው ሰራሽ ስህተት የተከሰቱ ናቸው።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ቀውስና ሠደድ እሳት

የኢትዮጵያ ምዕራባዊ ክፍል የሆነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰሃራ በረሃ መስፋፋትን ገድግዶ የያዘ የደን ሽፋን ያለበት ቀጣና ነው። ለዚህም አረንጓዴው ግድግዳ የሚሰኘው። ይህ ክልል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በየወቅቱ የሚከሰቱ ግጭቶች መልከ ብዙ ቀውሶችን አምጥቷል። በክልሉ ዞኖች አንዱ በሆነው የንፁሃን ግዲያና ግጭት በተፈታተነው መተከል ዞን ተገኝቼ እንደታዘብኩት (ጥቅጥቅ ጫካዎችን የማየት እድል ባይገጥመኝም) በርካታ ከባቢዎች በእሳት ነበልባል ተጠብሰው ቅሪቶች ሆነዋል። ከአካባቢው ነዋሪዎች እንደሰማሁት ከሆነ ለቤት ክዳን የሚያገለግሉ የጫካ ሳሮች በሰደድ እሳት ተቃጥለዋል። ይህም ምንም እንኳ ዜጎች የመፈናቀልና የሞት አደጋ ሰለባዎች ቢሆኑም በአካባቢው ተመልሶ የእርሻ ስራዎችን ለማከናወን /ካምፕ ለመስራት/ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው። ግጭቶች ለደን ሰደድ እሳት መለኮስ መንስኤ ናቸው የሚለውን የዶክተር ምናሴን ሃሳብ አንዱ ማረጋገጫው ይሄው የመተከል ዞን ትዝብቴ ጉዳይ ነው።

አርብቶና አርሶ አደሮች ደኖችን ለዱር እንስሳት አደን ያቃጥላሉ። አዲስ ተጨማሪ ለም መሬት ለማግኘትም በርካቶች ወድመት ያደርሳሉ። በሽታዎችን ለመከላከልና ለእንስሳት አዳዲስ ሳሮችን ለማብቀል ሲባልም ደኖች የእሳት እራት ይሆናሉ። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ሳር ምድር በሚበዛባቸው ቤኒሻንጉልና ጋምቤላ ክልሎች አስቸጋሪ አረሞችን ለማጥፋት እሳት ይለቀቃል፣ ይህን በአግባቡ ካልተቆጣጠሩት ደኖችን ወደሚበላ ሰደድነት ይለወጣል። ከሰል በብዛት ከሚከሰልባቸው ስፍራዎች አንዱ መተከል ዞን ነው፤ የጫካ ማርም በከፍተኛ ደረጃ ይመረትበታል። ይህም ለእሳት መነሻ ሌላው መንስኤ መሆኑ አይቀሬ ነው። ጉዳዩን የሚመለከተው የክልሉ መስሪያ ቤት የስራ ሃላፊ በጉዳዩ ላይ ብንጠይቃቸውም በክልሉ ባለው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር በደኖች ደህንነት ላይ ስራዎች እንዳልተሰሩ ገልጸዋል።


የሰደድ እሳት መፍትሔዎች ምንድናቸው

በሰደድ እሳት ሳቢያ በየጊዜው የሚያደርሰው ምጣኔ ሀብታዊ፣ ስነ ሕይወታዊና የንብረት ጉዳት እየከፋ መጥቷል። በኢትዮጵያ ላለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት የደን ቃጠሎን ለመከላከል ትኩረት እየተሰጠው መጥቷል የሚል እምነት አላቸው-ዶክተር ምናሴ። ሰደድ እሳት የተፈጥሮ ሃብት ለአብነትም በውሃ ሃብት ብክለት፣ የአየር ንብረት መዛባት፣ የዱር እንስሳት ክፉኛ ይጎዳል።

በሠደድ እሳት መከላከል ሶስት አንኳር መከላከል ደረጃዎችን ያነሳሉ። የመጀመሪያው ቅድመ መከላከል ነው። የደን ቃጠሎ ጉዳይ እንደ ጤና ጉዳይ መታየት እንዳለበት ይናገራሉ። ከቅድመ መከላከል ስራዎች ቃጠሎ ከመድረሱ በፊት የግንዛቤና የማስተማር ስራዎችን ማስፈጸም፣ የህግ ማዕቀፍ አውጥቶ ገቢራዊ ማደረግና ተቀጣጣይ ነገሮችን መለቃቀም ወይም የእሳት ቀይ መስመር ማስመር ተጠቃሽ ናቸው። እሳት ለመነሳት የሚቀጣጠል ቁስ፣ አያያዥ ኦክስጅንና አቀጣጣይ እሳት (ለምሳሌ ክብሪት ወይም የማር ቀፎ) ሶስት ነገሮች እንደሚያስፈልጉ ገልጸው፣ ከሶስቱ አንዱን ካስወገድን ቀድሞ መከላከል ያስችላል። በዚህም ‘ታሞ ከመማቀቅ አስቀድም መጠንቀቅ’ እንዲሉ ቅደመ መከላከል ለደን ሰደድ እሳት መከላከል አይተነኛ መፍትሄ ነው ባይ ናቸው።

ሁለተኛው ስልት ደግሞ እሳት ከመነሳቱ ወዲያውኑ የሚደረጉ እርምጃዎች ናቸው። ‘ሳይቃጠል በቅጠል’ እንዲሉ። ሶስተኛው ደረጃ ግን ሰደድ እሳቱ ከተነሳ ጉዳት ማስከተሉ ስለማይቀር ጉዳቱን ለመቀነስ የውሃ ማቆሪያዎችን መስራት፣ ማማ ማዘጋጀትንና መሰል ተግባራትን በመከወን የእሳቱን ጉዳት የመቀነስ ደረጃ ነው።

እንደ ዶክተር ምናሴ ማብራሪያ ባለፉት ሶስት ዓመታት ሰደድ እሳትን የሚመለከት የስራ አመራር (የእሳት ቁጥጥር ስርዓት) ዕቅድ የማዘጋጅት ጅምሮች አሉ። እሳት በሚነሳባቸው ወቅቶችና በማይነሳባቸው ጊዜያት ማድረግ ስላለማቸው ክንውኖች የትግበራ ዕቅድን ያቀፈ ነው። ይህ የደን ስራ አመራር መርሃ ግብር ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በቃፍታ ሽራሮ ብሄራዊ ፓርክ መዘጋጀቱና ለትግበራ በዝግጅት ላይ ስለመሆኑ ገልጸዋል። በዚህ ዓመት ደግሞ በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ገቢራዊ ለማድረግ ሰነዱ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል። በቀጣይ በሌሎች ፓርኮችም ላይ ይቀጥላል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተመሳሳይ በሰደድ እሳት ሁኔታ፣ ጉዳቱና መፍትሄዎችን ያካተት ጥናት ላለፉት ሶስት ዓመታት ጥናት እየተደረገ መሆኑንም ያነሳሉ። በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ በጋምቤላ ጥናቱ ይጀምራል። ጥናቶች ሰደድ እሳትን ከመቆጣጠር በተጨማሪ ደኖችን ሳያወድም መጠቀም በሚያስችል ደረጃ የተባይ ማጥፊያ፣ ጨሌ ሳር ማብቀያና ለሌላ ጥቅም ለማዋል የሚያስችል መርሃ ግብር ለመንደፍ ያግዛሉ። 

ኢትዮጵያ እስካሁን ብሔራዊ የእሳት መከላከያ ፖሊሲ የላትም። የደን ፖሊሲም ቢሆን በቅርቡ የወጣ ነው። በሰደድ እሳት ያቀጣጠለ ሰው እስከ 5 ዓመት እስራት እንደሚቀጣ ቢደነገግም የተጠናከር የህግ ማዕቀፍ ግን የላትም። በሌሎች አገሮች ሰደድ እሳትን የሚቆጣጠሩበት አንዱ ስልት ፖሊሲና የፖሊሲ ማስፈጸሚ የህግ ማዕቀፎች አሏቸው። የሰደድ እሳት መከላከል ፖሊሰ የዘገየው በቅድሚያ የደን ፖሊሲ ማስፈጸሚያ የህግ ማዕቀፎች መጽደቅ ስላለባቸው እንደሆነ ያብራረሉ። የደን ፖለሲ ማስፈጸሚያ ህግና አዋጆች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርተዋል። ውሳኔ አግኝቶ ከጸደቀ ለሰደድ እሳት ፖሊሲም መነሻ ሆኖ ተያያዥ ህጎች እንዲረቀቁ እድል እንደሚፈጠር ገልጸዋል።

እንደ መውጫ

የአየር ንብረት መዛባት ገፈትን እየቀመስን ነው። አየር ንብረቱ መዛባቱ ዓለምንም እያዛባ መጥቷል። ኢትዮጵያ ደግሞ ዙሪዋን በርሃማና ቆማላ ስርዓተ ምህዳር የተከበበች ናት። የደን ቃጠሎን መከላከልና አለመጠበቅ ደግሞ አደጋው የከፋ ነው። የደን ሃብት መመናመን ‘የከሸፈ ስርዓተ ምህዳር’ ፈጥሯል። ለበርሃማነት መስፋፈት ብቻ ሳይሆን በረዷማ ቦታዎችን ያቀልጣል። እናም ኢትዮጵም ዙሪዋን መጠበቅ አለባት። ትልቁ የአረንጓዴ ግድግዳ የሚሰኘው የደን ሃብት ከሞዛምቢክ ጀምሮ ኢትዮጵያን ያካተተ ደን የሰሃራ በርሃማነትን መከላከያ ተፈጥሮ ሀብት አለ።ዛፍ በመትከል የደን ግድግዳ መስራት በአፍሪካ ደረጃ ግብ ተቀምጧል። ይህን የደን ሃብት ከሠደድ እሳት መጠበቅ ተገቢ ነው። 

ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር የምትጋራቸው የደን ሃብቶች እንዷላት የሚቅሱት ዶክተር ምናሴ፣ ድንበር ተሻጋሪ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ስራዎች አስፈላጊ እንደሆኑ ይናገራሉ። ጥበቃዎችን ማጠናከረ ልማትን ማሳለጥ ተገቢነት አለው። ለምሳሌ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን አዋሳኝ ያሉ የኢትዮጵያ ደኖች ድንበር ዘለል ስራ አመራር ቀርጾ መተግበር የሚያሻቸው ናቸው። በቢሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የሚዋሰነው የአልጣሽ ፓርክ ከሚጎራበተው የሱዳኑ ዲንደር ፓርክ፣ በተከዜ ሸለቆ የሚገኘው የቃፍታ ሽራሮ ከኤርትራ፣ ከማዕለላዊ አፍሪካ ተነስቶ ደቡብን በማቋረጥ ከጋምቤላ ጋር የሚዋሰን የደን ሃብትን ደግሞ ከጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ጋር አስተሳሰሮ ጥበቃ ማድረግ ይገባል። በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክም ከአዋሳኞቹ ጋር ቅንጅታዊ ስራዎች መተግበር ግድ ይገባል። ድንበር ተሻጋሪ ደኖች የድንበር ዘለል ሰደድ እሳት እራት እንዳይሆኑ በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል።


በምስራቅ አፍሪካ አጠቃላይ የደን ሃብት 134 ሚሊዮን ሄክታር እንደሚሸፍን ይገመታል። በየዓመቱ የውድመቱም መጠን ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል። የኢትዮጵያ ጎረቤት ሱዳን በየዓመቱ በአማካይ 1 ሚሊዮን ሄክታር ደን በተለያዩ ምክንያቶች የሚወድምባት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሀገር መሆኗን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም