አዲስ አበባን የሚያወድም ጊዜው ያለፈበት የኬሚካል ክምችት አለ በሚል የተሰራጨው መረጃ ሀሰት ነው- የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት

78

ሚያዚያ 2/2013 (ኢዜአ) "አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ የሚያወድም ጊዜው ያለፈበት የኬሚካል ክምችት አለ በሚል በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ የትስስር ገፆች የተሰራጨው መረጃ የተዛባና የተሳሳተ በመሆኑ፤ ህብረተሰቡ የዕለተ ተዕለት እንቅስቃሴውን ያለስጋት እንዲያከናወን" ሲል የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አሳሰበ።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጉዳዩን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በትናንትነው ዕለት የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የሰጠውን ጋዜጣዊ መግለጫ "አንዳንድ መገናኛ ብዙሃንና የማህበራዊ የትስስር ገፆች አዛብተው አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ ማውደም የሚችል ጊዜው ያለፈበት የኬሚካል ክምችት አለ በማለት ሃሰተኛ መረጃ በማሰራጨት በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የደህንነት ስጋት ለመፍጠር ሲሞከር ነበር" ብሏል።

ተከማችቷል የተባለው ኬሚካል የኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት ለነቀዝ ማጥፊያ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳስገባው ያስታወሰው መግለጫው፤ በአጠቃቀምና በአያያዝ ጉድለት እንዲሁም በቸልተኝነት ምክንያት በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ሳይንሳዊ ሂደትን ተከትሎ ለማስወገድ በመንግስት በኩል እየተሰራ መሆኑን አመልክቷል፡፡

ኬሚካሎችም ሆኑ ተቀጣጣይ ክምችቶቹ ለታለመለት አላማ ከመዋላቸው በፊትና በኋላ አስፈላጊው ጥበቃና ቁጥጥር እንደሚደረግ የጠቆመው መግለጫው፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገርም የሚወገዱበት ስርዓት መኖሩን አስታውቋል፡፡

ይሁንና በኤጀንሲው የተሰጠውን ጋዜጣዊ መግለጫ መነሻ በማድረግና አዛብተው በማቅረብ፤ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃንና የማህበራዊ ትስስር ገፆች አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ ማውደም የሚችል ጊዜው ያለፈበት የኬሚካል ክምችት በተለምዶ ላፍቶ በሚባለው አካባቢ አለ የሚል ሃሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ህብረተሰቡን የማደናገርና ከዚያም ባለፈ የደህንነት ስጋት ለመፍጠር እየሞከሩ ነው ብሏል አገልግሎቱ በመግለጫው፡፡ 

በመሆኑም የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አለ የተባለው የኬሚካል ክምችት ለከተማዋ ነዋሪዎች የደህንነት ስጋት የሚፈጠር አለመሆኑን ከሚመለከታቸው አካላት ያረጋገጠ ሲሆን፤ ህብረተሰቡ በተሰራጨው የተሳሳተ መረጃ ሳይወናበድ የዕለተ ተዕለት እንቅስቃሴውን ያለምንም ስጋት እንዲያከናውን ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም