በድሬዳዋ የኮቪድ ናሙና ከሚሰጡ ሰዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ቫይረሱ እየተገኘባቸው ነው

74

ሚያዚያ 2 /2013 (ኢዜአ) በድሬዳዋ በየቀኑ የኮቪድ ናሙና ከሚሰጡ ሰዎች በአማካይ ከግማሽ በላይ በሚሆኑት ቫይረሱ እየተገኘባቸው መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮ ሃላፊዋ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ ለኢዜአ እንደገለጹት በድሬዳዋ የኮቪድ-19 ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

በየቀኑ የሳምባ ምችና የመተንፈሻ አካል ሕመም ላጋጠማቸው ከመቶ ለማይበልጡ ሰዎች ምርመራ እንደሚደረግና ከ50 በመቶ የሚልቁት የኮሮና ቫይረስ እንደሚገኝባቸው ገልፀዋል።

ይህም የኮሮና ቫይረስ በኅብረተሰቡ ውስጥ በስፋት እየተሰራጨ መሆኑንና ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያል ነው ያሉት።

ባለፈው አንድ ወር ብቻ 20 የሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች በኮቪድ ሳቢያ ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን ይህም ከቫይረሱ መከሰት ጀምሮ የአንድ ወሩ የሟቾች ቁጥር ከዚህ ቀደም ከተከሰተው ከእጥፍ በላይ ነው።

ቫይረሱ ከተከሰተ ጀምሮ በከተማዋ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር 47 ሲሆን 20ዎቹ ባለፈው ወር ብቻ መሞታቸውን ተናግረዋል።

 በዚህም በከተማ አስተዳደሩ የሞት ምጣኔ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

በከተማዋ ያለው ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ ከአራት ያልበለጠ ቢሆንም መሳሪያውን እየተጠባበቁ ያሉ 19 ሰዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

የቢሮ ሃላፊዋ የአካባቢው ማኅበረሰብ የኑሮ መስተጋብርና ንክኪ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እንዲባባስ ማድረጉን ጠቁመዋል።

በዚህ ሳቢያ ቫይረሱን የመከላከል አስገዳጅ መመሪያው እንዲተገበር መደረጉንና በትናንትናው ዕለት ብቻ  መመሪያውን በተላለፉ ስድስት ሆቴሎችና ግሮሰሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልፀዋል።

ኅብረተሰቡ እየተባባሰ የመጣውን የኮቪድ ስርጭት ለመከላከል የወጡ መመሪያዎችን በመተግበርና የግል ንጽህናውን በመጠበቅ በሽታው ከሚያስከትለው የከፋ ችግር ራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

በተለይ የተቋማት ሃላፊዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት መመሪያዎችን በአግባቡ በመተግባር ተገልጋዮችን ማስተናገድ እንዳለባቸውም እንዲሁ።

ጤና ቢሮው የምርመራ አቅምን ለማሳደግና ከግል ሆስፒታሎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የችግሩን አሳሳቢነት ለመቀነስ እየሰራ መሆኑንም ሃላፊዋ ጠቁመዋል።

በከተማ አስተዳደሩ 54 በመቶ ለሚሆኑ የሕክምና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሲጪዎች የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት መሰጠቱን ገልፀዋል።

ዕድሜያቸው ከ55 በላይ ለሆኑና ተጓዳኝ በሽታ ላለባቸው ሰዎች መመሪያው በሚያዘው መሰረት ክትባት መስጠት መጀመሩንም አክለዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮ 32 ሺህ 198 ሰዎች የተመረመሩ ሲሆን 3 ሺህ 879 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም