በአዲስ አበባ የፍጥነት መቆጣጠሪያ ጉብታዎች ከፍ በማለታቸው በመኪና ላይ ጉዳት እያስከተሉ እንደሆነ አሽከርካሪዎች ገለጹ

114
አዲስ አበባ ሀምሌ 23/2010 በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች የተሽከርካሪ ፍጥነትን ለመቆጣጠር በአስፋልት ጎዳና ላይ የሚሰሩ ጉብታዎች ከፍታቸው ከመጠን ያለፈ በመሆኑ በመኪና የውስጥ አካላት ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን አሽከርካሪዎች ገለጹ። ጉዳቱ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እየዳረጋቸው እንደሆነም አመልክተዋል። የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በበኩሉ፤ ''የፍጥነት መቀነሻዎቹ በጥናት ላይ ተመስርተው በመሰራታቸው በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ይደርስ የነበረው ጉዳት እንዲቀንስ አድርጓል'' ብሏል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አሽከርካሪዎች እንደገለጹት፤ ለተሽከርካሪ ፍጥነት መቆጣጠሪያ ተብለው የተሰሩ ጉብታዎች አደጋ ለመቀነስ የራሳቸው የሆነ ጥቅም ያላቸው ቢሆኑም ከፍታቸው ከመጠን ያለፈ በመሆኑ በተሽከርካሪዎቻቸው ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው። ጉብታው ከፍ በማለቱ መኪናዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ ለተጨማሪ ወጪ እየተዳረጉ መሆኑን አመልክተዋል። በተለይም ጉብታዎቹ ምልክት ስለሌላቸው መንገዶችን በደንብ የማያውቁ አሽከርካሪዎች በፍጥነት እያሽከረከሩ ለጉዳት እየተጋለጡ እንደሆነ ጠቁመዋል። እንዲህ አይነት ስራ ሲሰራ በጥናት ላይ ተመስርቶ መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል። አቶ እስማዬል አላቦ ስድሰት ኪሎ አካባቢ ያገኘነው ሹፌር  አንዳንድ የፍጥነት መቆጣጠሪያዎች  በጣም ክፍ ያሉ በመሆናቸው  እስኮፓ እየመታብን ተቸግረናል  ዘይት እያፈሰሰብን  ነው፡፡  እስከ 25ሺህ ብር ወጪ  ሊያወጣ ይችላል የሚመለከተው አካል የፍጥነት መቆጣጠሪያዎች መልካም ነው ግን አነስ ቢል የተሻለ ይሆናል ሲል አስተያቱን ሰጥቷል፡፡ ወጣት ዘላለም ፍሰሃ በበኩሉ ብሬከሮቹ መሰራታቸው ጥሩ ነው ግን ይሁንና ጥናት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡ አዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የህዝብ ግኑኙነት ዳሬክተር  አቶ ታመነ በሌ እንደገለጹት፤ ፍጥነት መቀነሻ ጉብታዎቹ ሲሰሩ ጥናት ላይ የተመሰረተና  ከተሰሩ በኋላም በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ይደርስ የነበረውን ጉዳት እንዲቀንስ አድርገዋል። ይሁንና  የተሰሩት  ስራው የመጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን የተጠቀሱተ ቦታ ላይመ ሆነ  ሌሎች  አካባቢ ያሉት በድጋሚ በማየት ማስተካከያ እንደሚደረግባቸውና በቀጣይ የሚሰሩት ላይ ጥንቃቄ  እናደርጋለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም