ተማሪዎችን ምን ማሰብ እንዳለባቸው ሳይሆን እንዴት ማሰብ እንዳለባቸው አስተምሯቸው - ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

58

መጋቢት 30 / 2013 (ኢዜአ) መምህራን እውቀትና መልካም ሥነ-ምግባር የተላበሱ ብቁ ዜጎችን በማፍራት አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።

በአገር አቀፍ ደረጃ ሥራ ላይ ያሉ 143 እንዲሁም በጡረታ የተሰናበቱ 40 መምህራን እውቅና ተሰጣቸው።

በእውቅና መርሃ ግብሩ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፤ "ለአገር ውለታ የዋሉ ሰዎችን ማክበርና እውቅናም መስጠት ሊለመድ ይገባል" ብለዋል።

መምህርነት የሁሉም ሙያዎች አባት መሆኑን ገልጸው፤ በዘርፉ ተሰማርተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ መምህራን ምስጋና ችረዋል።

መምህራን ብቁ ዜጋ የመቅረጽ አገራዊ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይም ሕጻናትና ወጣቶችን በወቅቱና በአግባቡ መኮትኮት ከምጊዜውም በላይ ቁልፍ ተግባር መሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

"በአጉል መንገድ ያደገን ዛፍ ለማቃናት ከመስበር ሌላ ስለማይቻል ሁሉን ነገር አስቀድሞ መሥራት የማይታለፍ ሁኔታ ነው" ሲሉም አስረድተዋል ፕሬዚዳንቷ።

ስለዚህም መምህራን በራሱ የሚተማመን፣ የሚያስብ፣ በሃሳብ ልዕልና የሚያምን፣ አማራጭ ሃሳብ የሚያቀርብ ዜጋ ማፍራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ "ከእኔ አውቅልሃለው አስተሳሰብ የተላቀቀ፣ ለሌላው የሚገባውን ቦታ የሚሰጥ፣ አለመግባባትን በውይይት ብቻ መፍታት እንዳለበት የሚያምን ዜጋ ያስፈልገናል" ነው ያሉት።

ለሕግ ተገዥና የሰውን ልጅ መሠረታዊ የመኖር መብትን የሚያከብርና ለዚህም የሚሟገት አካታች አስተሳሰብ ያለው ዜጋ ማፍራት እንደሚያስፈልግም አክለዋል።

በድምሩ መምህራን ተማሪዎች ምን ማሰብ እንዳለባቸው ሳይሆን እንዴት ማሰብ እንዳለባቸው የማስተማር አደራቸውን መምህራኑ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጓዳኝ ዓለም የደረሰበትን ደረጃ ከግምት ያስገባ እውቀትና ክህሎት ያለው ዜጋ ማፍራትም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው መምህራን ለአገሪቷ በተለያዩ ዘርፎች በተዘዋዋሪ ላበረከቱት አዎንታዊ አስተዋጽኦ 'ክብር ይገባቸዋል' ብለዋል።

መመህራን አሁንም በትውልድ ላይ የሚያሳድሩትን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባት ለመምህራን አቅም ግንባታ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

"የመምህራን ልማትና ሥልጠና ሥርዓት መሰረትም ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ዲፕሎማ ዝቅተኛ የመምህራን የትምህርት ዝግጅት ሆኖ እንዲተገበር እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ለአንደኛና ለመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ዲግሪ፤ ለሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የማስተርስ ዲግሪ እንዲሆን እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የመምህራን የሥራ ላይ ምዘና እንደሚሰጥና አንድ መምህር አንድ የትምህር አይነት ብቻ እንዲያስተምር ለማድረግ ትኩረት ተደርጓል ሲሉ ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም