ከሚሌ ወደሎግያ ሲጓዘ የነበረ ሲኖትራክ ገልባጭ መኪና ተገልብጦ አንድ ሰው ሲሞት ስምንት ሰዎች ቆሰሉ

83
ሰመራ  ሀምሌ 23/2010 አፈርና  አስር ሰዎችን ጭኖ ከሚሌ ወደሎግያ ሲጓዘ የነበረ ሲኖትራክ ገልባጭ መኪና ተገልብጦ አንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ በሌሎች ስምንት ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ። የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሺን የትራፊክ አደጋ መንስኤ ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ ምክትል ኮማንደር መሃመድኑር አደም እንዳሉት ዛሬ የመኪና አደጋ የደረሰው የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ-3-61127 (ኢት) የሆነ ሲኖትራክ ተሽከርካሪ ከሚሌ ወረዳ ልዩስሙ ሀርሲስ ቀበሌ አፈርና አሥር ሰዎችን ጭኖ ወደሎግያ ሲጓዥ በመገልበጡ ነው። እንደ ምክትል ኮማንደር  መሃመድኑር ገለጻ አደጋው ከቀኑ 5፡00 ላይ የደረሰው ተሽከርካሪው ሎግያ ከከተማ ከመድረሱ በፊት ልዩስሙ "ሰለሜ" በሚባል ቦታ ሲሆን በአደጋውም የአንድ ሰው ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ ሌሎች ስምንት ሰዎች ደግሞ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ለጉዳት ከተዳረጉ ሰዎች መካከል 4ቱ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ሌሎች 4 ሰዎች ደግሞ ቀላል ጉዳት ቀሪው አንድ ሰው ምን ጉዳት እንዳልደረሰበት ተናግረዋል። ምክትል ኮማንደሩ እንዳሉት ተጎጂዎቹ የተሻለ ህክምና እንዲያገኙ በሚል ወዴዱብቲ ሪፈራል ሆስፒታል ተልከው ሕክምናው እየተደረገላቸው ይገኛሉ። የመኪናው አሽከርካሪ በህግ ቁጥጥር ስር ዉሎ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን ገልጸው፣ ሰውና የግንባታ እቃን  ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ አንድ ላይ መጫን በህግ እንደሚያስጠይቅ አስረድተዋል፣    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም