በኢትዮጵያና ኳታር መካከል የወጪና ገቢ ንግድ ለማመጣጠን ንግድና ኢንቨስትመንት ማሳደግ ይገባል ተባለ

1073

አዲስ አበባ ሀምሌ 23/2010 በኢትዮጵያና ኳታር መካከል ያለውን የወጪና ገቢ ንግድ ለማመጣጠን በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ማሳደግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ገለጸ።

በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ 16 ዓለም አቀፍ የኳታር ድርጅቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ዛሬ በአዲስ አበባ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መልአኩ እዘዘው እንዳሉት፤ በኢትዮጵያና ኳታር መካከል ያለው የወጪና ገቢ ንግድ መጠን ሰፊ ልዩነት አለው።

ባለፉት አስር ዓመታት እንኳን ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር ከፈጸመችው የወጪ ንግድ ያገኘቸው 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ከኳታር ያስገባቸው ደግሞ 172 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የውጪና ገቢ ንግድ ምጣኔ ልዩነት ለማጥበብ የኳታር ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማሩ መንግስት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ነው ብለዋል።

በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ መጠን የተጋገነ ቢሆንም በድምሩ ዝቅተኛ መሆኑን የገለጹት ኢንጂነር መልአኩ ስፋቱን ለማጥበብና መጠኑን ለማሳደግ በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ባለሃብቶች ከኳታር ባለሃብቶች ጋር በአዲስ ምዕራፍ የተሻለ ግንኙነት በመፍጠር የሁለቱን አገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት የማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቢዝነስና ዲያስፖራ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሃብቶች ያላትን ምቹ አጋጣሚ ኳታር ልትጠቀምበት ይገባል ብለዋል።

ኳታር ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስትራቴጂክ አጋርነት ተጠቅማ ባለሃብቶቿን በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዘርፍ በማሰማራት የሁለቱን አገራት ኢኮኖሚያዊ ትብብር ማሳደግ እንደምትችልም ገልጸዋል።

አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ኢንዱስትሪ፣ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ፣ ሃይል፣ ማዕድንና ተፈጥሮ ሃብት፣ ሆቴልና ቱሪዝም፣  ኮንስትራክሽንና ሌሎችም ዘርፎች የኳታር ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መሰማራት የሚችሉባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ዘጠኝ የኳታር ድርጅቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የሁለቱ አገሮች የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ከዚህም በላይ ማደግ ይኖርበታል ብለዋል።

የኳታር ልማት ባንክ ዋና ዳይሬክተር ሀሰን ካሊፋ አል ማንሶሪ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዷ የግል ዘርፉን ለማበረታታት ማለሟ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቷን ያሳድገዋል ብለዋል።

ይህም ስትራቴጂክ አጋሯ ኳታርን ጨምሮ ሌሎች የውጭ ድርጅቶች በኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።

 እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ 2016 የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ሲሆን በአንጻሩ የኳታር 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።