እግር ኳስ የማንነትና የብሄር መልዕክት ማስተላለፊያ ሊሆን አይገባም-ደጋፊዎች

70
 አዲስ አበባ  ሀምሌ 23/2010 እግር ኳስ የማንነትና የብሄር መልዕክት ማስተላለፊያ ሊሆን አይገባም ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የስፖርት ቤተሰቦች ተናገሩ። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ ዋንጫ ለማንሳትና ላለመውረድ የሚደረግ ትንቅንቅ እጅግ አጓጊ ፉክክር እያስተናገደ መጥቷል። ይሁንና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ስፖርታዊ ጨዋነቱን እየለቀቀ ሥርዓት አልበኝነትን ማንጸባረቅ ከጀመረም ውሎ አድሮ ሰነባብቷል። በስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት በስታዲየሞች በደጋፊዎች መካከል በሚሰከስ ሁከትና ብጥብጥ ሳቢያም በርካቶችን ለአካል ጉዳት ብሎም ለህልፈተ-ህይወት እየዳረገ ይገኛል። ከዚህም ባሻገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፖርት ሜዳ ላይ የአገሪቱን ፖለቲካዊ መልክ የሚያንፀባርቁ ሁኔታዎችን የማራመድና የዘረኝነት መልዕክት እየተላለፉ በመሆናቸው ስፖርቱ መሠረቱን እያጣ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የእግር ኳስ ቤተሰቦች ይናገራሉ። እግር ኳስ ፍጹም ከፖለቲካና ከዘረኝነት የጸዳ፣ በሌሎች የዓለም አገራት ላይም ከመዝናኛነት ባሻገር የተጣሉትን የሚያስታርቅ ነጻና የሰላም መድረክ እንጂ የማንነት መገለጫ ሊሆን አይገባም ሲሉም ተናግረዋል። ምንም እንኳን የዚህ አይነቱን ተግባር በስፖርት ሜዳ ላይ የሚያራምዱ ደጋፊዎች ሁሉም ባይባሉም ተግባሩን የሚያሳዩት ግን ድርጊቱ አላስፈላጊና የእግር ኳስ ወዳዱን ህብረተሰብ የሚጎዳ ብሎም እግር ኳሱን ወደኋላ የሚያስቀረው መሆኑን ተረድተው ሁሉም ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ብለዋል። በተለይም የዚህ አይነት ድርጊቶችንና ጥፋቶችን በማረምና በማስተካከል ረገድ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ቀዳሚውን ድርሻ በመውሰድ ለሚቀጥሉት ጊዜያት ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚገባውም ጠቁመዋል። ቢንያም ታምራት የተባለው ስፖርቱ ቤተሰብ እንደተናገረው ከማንነት ጋር በተያያዘ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ባለፉት አመታት አየታየ እንደሚገኝ በተለይ የክለቦች ፉክክሩ መጠናከሩ ተከትሎ ችግሩን በስፋት እየታየ እንደሚገኝ ተናግሯል ዘንድሮ በስፖርታዊ ጨዋነትም ባፈነገጠ መልኩ በከፍተኛ ሁኔታ የታየበት መሆኑን የተናገረው ቢኒያም ያለፈው አልፏል ከዚህ በኋላ ፌዴሬሽኑ ጥሩ ስራ ሰርቶ  ስህተቶች  ይስተካክላል ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ መስፍን ተስፋዬ የተባለው ሌላው የስፖርት ቤተሰብ በኳሱ ላይ እየታየ ያለውን የዘረኝነት ችግርና የስፖርታዊ ጨዋነት  መጎደል ለማስተካከል ፌድሬሽኑና አመራሩ ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝቧል፤፤ ችግሩን ለመፍታት ከለቦችም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ከፌድሬሽኑ ጋር መምከርና በጋራ መስራት ይገባቸዋልም  ብሏል፡፡ በስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ብዙ ደጋፊዎች ተጎድተዋል ከክልል መምጣትም ሆነ ወደ ክልል መሄድ ያልተቻለበት ሁኔታ ነው ያለው የሚለው ደግሞ ሰለሞን ተሾመ የተባለው የእግር ኳስ ቤተሰብ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ ራሱን አርሞ አስተካክሎ ካልመጣ ድረስ የሚቀጥለው አመት እንዲያውም የከፈ ነው የሚሆነው ምክንያቱም እግር ኳሱ እየተመራ ያለው በእግር ኳሳዊ ስሜት ስላልሆነ  ሲልም  ጨምሮ ተናግሮል 16 ክለቦች የተሳተፉበት የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር በጅማ አባጅፋር ሻምፒዮንነት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው። ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ወልድያና አርባምንጭ ከተማ  ደግሞ ወደ ብሔራዊ ሊግ የወረዱ ክለቦች ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም