በዞኑ በተገነቡ የንጸህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ከ16 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል -መምሪያው

49

ደሴ፣ መጋቢት 29/2013 (ኢዜአ ) ባለፉት ስምንት ወራት በተገነቡ የንጸህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ከ16 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን የደቡብ ወሎ ዞን ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ መምሪያ አስታውቀ፡፡

የንጹህ መጠጥ ወሀ አገልግሎት በአቅራቢያችን በማግኘታችን በእለት ተእለት ያጋጥመን የነበረው የኑሮ ጫና ተቃሎልናል ሲሉ የወረኢሉ ወረዳ ነዋሪዎች ለኢዜአ ተናግረዋል ።

የመምሪያ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ሽመልስ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ  የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ለማሳደግ ከባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።    

በበጀት ዓመቱ ከመንግስት፣ ከረጂ ድርጅቶችና ከህብረተሰቡ በተገኘ 20 ሚሊዮን ብር ወጭ 130   የውሃ ተቋማት ለመገንባት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን አስታውሰዋል።

ባለፉት ስምንት ወራት 58 የጎለበቱ ምንጮች ጨምሮ  አነስተኛና መካከለኛ ጥልቅ ጉድጓዶች ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል።

"በተቋማቱ ከ16 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በአቅራቢያቸው የንጹህ መጠጥ ውሀ አገልግሎት  ተጠቃሚ ሆነዋል " ብለዋል።

ተቋማቱ ከመሰረታዊ ጠቀሜታቸው ባለፈ ህብረተሰቡ ውሀ ፍለጋ የሚያባክነውን  ጊዜና የጉልበት  ለሌሎች ልማቶች  እንዲያውል ማስቻላቸውን ጠቅሰዋል።

የተገነቡት የመጠጥ ውሃ ተቋማት የዞኑን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን ከነበረበት ከ64 በመቶ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ወደ 67 በመቶ ከፍ ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት እንደሚያግዙ አመላክተዋል።

በወረኢሉ ወረዳ የቀበሌ 09  ነዋሪ ወይዘሮ አንሻ ሙስጠፋ በአካባቢያቸው የመጠጥ ውሃ ባለመኖሩ ረዥም ርቀት በመጓዝ ከወንዝ ቀድተው ለመጠቀም በመገደዳቸው ለጤና ችግር ከመጋለጣቸው በተጨማሪ ለጊዜና ጉልበት ብክነት ተዳርገው መቆየታቸውን አስታውሰዋል ።

"በአቅራቢያችን የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት ባለመኖሩ በሴቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድር ነበር "ያሉት ወይዘሮ አንሻ ዘንድሮ በተሰራላቸው የውሃ ተቋም አገልግሎቱን በአቅራቢያቸው በማግኘት ከችግራቸው መላቀቃቸውን ገልጸዋል ።

"የመጠጥ ውሃ ችግር ህብረተሰቡን ብቻ ሳይሆን እንስሳቶችን ጭምር ለስቃይ ዳርጎ  ቆይቷል" ያሉት ደግሞ በወረዳው የቀበሌ  07 ነዋሪ አቶ አስራት አብርሃ ናቸው።

"ችግሩን ለሚመለከተው አካል ብናሳውቅም ምላሽ በማጣታችን ከአንድ ሰዓት በላይ በእግር ተጉዘን የወንዝ ውሀ  በመቅዳት ለእለት ተእለት የኑሮ ጫና ስንዳረግ ቆይተናል" ያሉት አቶ አስራት ዘንድሮ አገልግሎቱን በአቅራቢያቸው በማግኘታቸው ከሚገጥማቸው ችግር መላቀቃቸውን አስታውቀዋል ።

"የተገነባልን የውሀ ተቋም እኛና እንስሳቶቻችን በቅርበት ውሃ እንድናገኝና ጤንነታችን እንዲጠበቅ፣ሴት ልጆቻችን ወደ ትምህርታቸው በጊዜ እንዲሄዱ አስችሏል" ሲሉ በውሀ በተቋሙ ያገኙትን ጥቅም ገልጸዋል።

በዞኑ በዚህ አመት ግንባታቸው የተጀመሩ የውሀ ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቁ አጠቃላይ ከ35 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም