ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት በኩል የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል ጽኑ ፍላጎት አላት- ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ

90

መጋቢት 29 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት በኩል የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል ጽኑ ፍላጎት እንዳላት የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለጹ።

በድርድሩ በታዛቢነት የሚሳተፉ አካላት የአደራዳሪነት ሚና እንዲኖራቸው በግብፅና ሱዳን የቀረበውን ሃሳብ ኢትዮጵያ ውድቅ ማድረጓንም ተናግረዋል።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶክተር ኢንጅነር) በአፍሪካ ህብረት በኩል በኮንጎ ኪንሻሳ የተደረገውን የሶስትዮሽ ድርድር በሚመለከት ዛሬ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር በአፍሪካ ህብረት በኩል እንዲቀጥል ጽኑ ፍላጎት እንዳላት አመላክተዋል።

በታዛቢነት የሚሳተፉ አካላት የአደራዳሪነት ሚና እንዲኖራቸው ግብጽና ሱዳን ያቀረቡትን ሃስብ ኢትዮጵያ ውድቅ ማድርጓን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በሚካሄደው የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረትና ደቡብ አፍሪካ በታዛቢነት እየተሳተፉ መሆኑ ይታወቃል።

በመሆኑም ግድቡ ድርድር ላይ እነዚህ በታዛቢነት የሚሳተፉ አካላት ከታዛቢነት ባለፈ የአደራዳሪነት ሚና እንዲኖራቸው ግብጽና ሱዳን ሃሳብ ማቅረባቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በድርድሩ ግብጽና ሱዳን ተጨማሪ ታዛቢ እንዲገባና ያሉትን የታዛቢዎች ሚና ለመቀየር ያሳዩትን ፍላጎት ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው በማሳወቅ ውድቅ አድርጋዋለች ብለዋል።

ግብጽና ሱዳን በተለይም ደቡብ አፍሪካን ከታዛቢነት ለማስወጣት ያደረጉትን ጥረትም መቃወሟን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ታዛቢዎቹ በድርድሩ ጣልቃ ሳይገቡ የታዛቢነት ሚናቸውን ለሁሉም ተደራዳሪዎች ጠቃሚ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ሶሶቱ አገሮች መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት በኩል የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል ጽኑ ፍላጎት እንዳላትም በድጋሜ አረጋግጣለች ብለዋል ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም