የጥናትና ምርምር ሥራዎች ወደ ተግባር በመለወጥ ረገድ ለውጥ መጥቷል -የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

93

መጋቢት 28/2013/ኢዜአ/ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ወደ ተግባር በመለወጥ ረገድ የተሻለ ለውጥ መምጣቱን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ተናገሩ።

የዘርፉ ያሉትን ፖሊሲዎች በማሻሻልና ለትምህርት ጥራት አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋትም አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር አፈወርቅ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ለውጡ እውን ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ የትምህርት ዘርፉን ለማሻሻል ልዩ ትኩረት ተስጥቶ እየተሰራ ነው።

በተለይም በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየትና ሁነኛ የመፍትሄ አቅጣጫዎች በማስቀመጥ የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅ ከፍትኛ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

የትምህርት ዘርፉ ፍትሃዊነት፣ አግባብነትና ተደራሽነት የተላበሰ እንዲሆን በርካታ የማሻሻያ ሥራዎች መከናወናቸውንም ነው የገለጹት።

በዘርፉ የሚደረጉ የምርምር ውጤቶችን ወደ ተግባር የመቀየር ስራም በስፋት በመከናወን ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጅማሮ 70 ዓመታት መቆጠሩን ያነሱት ሚኒስትር ድኤታው፤ በእነዚህ  ዓመታት  የምርምር  ስራዎች ቢካሄዱም ወደ ተግባር በመቀየር ረገድ ክፍቶች መኖራቸውን አውስተዋል።

ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ግን የጥናትና ምርምር ሥራዎች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ የተሰራው ሥራ ውጤት ተገኝቶበታል ብለዋል።

ለዚህም የጥናት ሥራዎቹ ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ለማስቻል ለተመራማሪዎቹ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ተግባራዊነት በመከታተል  ረገድም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በጤና፣ በግብርና እና በአፈር ጥበቃ ሥራዎች በኢትዮጵያዊያን የተሰሩ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ዓለም አቀፍ ተቀባይነተን አግኝተው እየተተገበሩ መሆኑን አብራተዋል።

በጤናው ዘርፍ በቆላማ አካባቢ የሚከሰተውን ሌሽማኒያ የተሰኘውን በሽታ ከአዲስ አበባ፣ አርባ ምንጭና ጎንደር ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ ባለሙያዎች ጥናት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የጥናት ውጤታቸውን ተከትሎም ለበሽታው ይሰጠው የነበረው የህክምና ጊዜ ከ30 ቀናት ወደ 17 ቀናት ዝቅ እንዲል ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

የጥናት ውጤቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን አግኝቷል ነው ያሉት።

በተጨማሪም በአፈር ጥበቃና በግብርና ሥራ ላይ አዳዲስ ዝርያዎች በምርምር መገኘታቸውን ገልጸው፤ ይህም በአርሶ አደሩ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን ጠቁመዋል።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በእንስሳት ተዋጽፆ ላይ ከዓመታት በፊት የጀመሩት የምርምር ሥራዎችም አዎንታዊ ውጤት አምጥተዋል ብለዋል።

በዚህም በቀን ሁለት ሊትር ወተት የሚሰጡ የላም ዝርያዎችን እንዲዳቀሉ በማድረግ በቀን 15 ሊትር ወተት እንዲሰጡ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

እነዚህንና ሌሎች በጅምር ላይ ያሉ የምርምር ውጤቶች ከህትመት በዘለለ በማኅበረሰቡ ዘንድ ችግርን እየፈቱ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በሌላ በኩል የዘርፉን የጥራት ችግር ለማቃለል በፖሊሲዎችና በአሰራር ላይ የተከናወኑት ማሻሻያዎች  ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን አብራርተዋል።

ለበርካታ ዓመታት ሲንከባለል የቆየውን የትምህርት ፍኖተ ካርታው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ማሻሻል መቻሉንም አንስተዋል።

በተጓዳኝም በተቋሙ የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ ውስጥ የሳይንስ ፖሊሲ፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋም ፖሊሲ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ ታቅዷል ነው ያሉት።

ማሻሻያው የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታን ያገናዘበና የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥም የጎላ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም