መገናኛ ብዙሃን አገራዊ አንድነት የሚያመጡ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለውጡን ሊያግዙ እንደሚገባ ተገለፀ

165
አዲስ አበባ ሐምሌ 23/2010 መገናኛ ብዙሃን በአገራዊ አንድነት ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለውጡን ሊያግዙ እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ገለፁ። ችግሮች ሲፈጠሩ ለመዘገብ ከመሯሯጥ ይልቅ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ቀድመው በመርሆችና በፖሊሲዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። መገናኛ ብዙሃኑ ያላቸውን ነፃነት ተከትለው ሕግን በማክበር በህዝብ አንድነትና በአገር ዕድገት ላይ ሊሰሩበት እንደሚገባም ጠቁመዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህር ዶክተር ተሻገር ሽፈራው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መገናኛ ብዙሃን የሚያቀርቡት ዘገባ እውነትነት ያለው ቢሆንም በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ የሚፈጥር እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። መገናኛ ብዙሃን በዘገባቸው ላይ እውነትን ቢይዙም ከኪሳራው ይልቅ ትርፉ ላይ ትኩረት በማድረግ ልዩነቶችን ከጋራ እሴቶች ጋር አጣምረው ማንፀባረቅ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል። በውስን አካባቢ የሚደመጡ እንደ ኤፍ ኤም የሬዲዮ ጣቢያዎች በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ዘገባ ሲያቀርቡ በአገራዊ አንድምታው ላይ መሠረት ማድረግ እንደሚገባቸው አስረድተዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ በበኩላቸው የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች አገራዊ አንድነትን ለማጎልበት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። ከህዝብ ስሜት ጋር መሄድ ብቻ ሳይሆን ህዝባዊ ስሜቱን በማጤን የተለያዩ ፓርቲዎች ፍልስፍናዎችን በማሳየት አገራዊ አንድነት ተጠናክሮ እንዲሄድና ሰላም እንዲሰፍን መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ሁልጊዜ እንደፈረስ ጋሪ ከኋላ መከተል እንጂ ከህዝቡ ቀደም ብሎ ፖሊሲ አመላካች መሆን አለማቻሉን ገልጸዋል። አሁን ላይ ባለው አገራዊ ለውጥ የህዝቡ ስሜት መነሳሳት እንዳለ ሆኖ መገናኛ ብዙሃን ከህዝቡ ስሜት ቀድመው ችግሮች እንዳይፈጠሩ መርሆችዎና ፖሊሲዎች ላይ መስራት እንዳለባቸው ያሳስባሉ። ዶክተር ተሻገር በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃኑ የአካባቢያቸውን ጭብጦች ሳይለቁ በየአካባቢው የሚፈጠሩ ቅራኔዎችንና ግጭቶችን የሚያጠፉ አጀንዳዎችን ደጋግመው በመስራት አገራዊ ለውጡን ማስቀጠል አለባቸው ይላሉ። በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሰልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ አብርሃ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም መገናኛ ብዙሃን በማወቅም ይሁን ካለማወቅ የህዝቦችን ተፈቃቅሮ የመኖር እሴት የሚሸረሽሩ ዘገባዎች አየር ላይ ሲያውሉ እንደነበር ጠቁመዋል። የህዝቦች ፍላጎት ሰላም መሆኑን በመገንዘብ ሚዲያዎች ህገመንግስቱንና የመገናኛ ብዙሃንን መረጃ ነፃነት አዋጅ መሰረት በማድረግ የህዝብንና የአገርን ጥቅም አስቀድመው ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል። አሁን ላይ በኢትዮጵያ የሚሰራጩ 26 የቴሌቪዥን እና ከ73 በላይ የሬዲዮ ጣቢያዎች እንዳሉ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሰልጣን የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም