ህብረተሰቡ ከሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳዎች በመራቅ የአገሪቱን ሰላም ሊጠብቅ እንደሚገባ ተገለጸ

676

መጋቢት 26/2013 ወጣቱ ትውልድ እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በአገሪቱ ከሚነዙ ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳዎች በመራቅ የኢትዮጵያን ሰላም ሊጠብቅ ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ተናገሩ።

ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፤ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሀዊ እንዲሆን የሁሉም አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት 85ኛ ዓመት የማይጨው ጦርነት መታሰቢያ ላይ ያነጋገራቸው የቀድሞ ሰራዊት አባላት አገር ለመገንባት እና ለማሳደግ ሰላም ቀዳሚውና ወሳኙ ጉዳይ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

የቀድሞ ኢትዮጵያ ሰራዊት አባል የሆኑት ኮሎኔል ዳንኤል ጉሳ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ስለሚታየውን የሰላም መደፍረስ አውስተዋል።

ወጣቱ ትውልድ እና ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል ከቀደሙ ስህተቶች ትምህርት በመውሰድና በጋራ በመቆም ለአገሪቱ ልማት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ይላሉ፡፡

አሁን ላይ ለጥፋት ኃይሎች መሳሪያ የሚሆኑት በአብዛኛው ወጣቶች ናቸው ያሉት ኮሎኔል ዳንኤል ትውልዱ የተለያዩ አጥፊ ኃይሎች የሚያራምዱትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ቆም ብሎ በማሰብ የአገሪቱን ሰላም ሊያስጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡

መንግስትም ሰላም ለማደፍረስ የሚሰሩ አጥፊ ኃይሎችን ለፍርድ የማቅረብ ስራውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

ወጣቶች የቀድሞ አባቶችና የሰራዊት አባላት የከፈሉትን መስዋእትነት አርአያ በማድረግ በአገራቸው ልማት ላይ የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የቀድሞው የመከላከያ ማህበር አባል የሆኑት አቶ ቀናኢ በዳዳ በበኩላቸው ወጣቱ ለበርካታ ዓመታት መርዛማ ነገር ሲረጭ መቆየቱን አውስተው ይህንን ለማስተካከል ጊዜ ይወስዳል ብለዋል፡፡

ወጣቶች የአገሪቱን ሁኔታ በመገንዘብና ታሪክን ወደኋላ በማየት እና በመጠየቅ ከቀደሙት አባቶቻችን የተረከቧትን አገር በሰላም ጠብቀው ሊያኖሯት ይገባል ብለዋል፡፡

ከቤተሰብ ጀምሮ ሁሉም ዜጋ ወጣቱ ትውልድ አላስፈላጊ ነገር ውስጥ እንዳይገባ የማንቃት ስራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

ወጣቱም የአገሪቱን እውነታ በገንዘብ ከተገዙ ኃይሎች ሳይሆን ከሀቀኛ የታሪክ አዋቂዎችና ምሁራን መረዳት ይኖርባቸዋል ሲሉ ያሳስባሉ፡፡

የቀድሞ ሰራዊት አባል ኢንስፔክተር ታደሰ አለማየሁም በአገሪቱ እየታዩ ያሉ ሁኔታዎችን ለማስተካከል ወጣቱ የአፍራሽ ኃይሎችን እኩይ ተልእኮ ተገንዝቦ አገር ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን እና እድገትን ለማፋጠን መንግስት ህዝቡን ያሳተፈ እንቅስቃሴ ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል፡፡


ይህ በእንዲህ እንዳለ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፤ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሀዊ እንዲሆን የሁሉም አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሜጀር ጀኔራል መርዳሳ ሌሊሳ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ ሰላሙን ጠብቆ የሚፈልገውን መምረጥ አለበት ብለዋል፡፡

ወጣቱ ይበጀኛልና እኔን መምራት ይችላል የሚለውን መሪ የሚመርጥበት በመሆኑ ምርጫው እንዲሳካ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት፡፡

መራጮችም የሚያምኑበትን ፓርቲ ለመምረጥ ትክክለኛ መንገድ ሊከተሉ፤ መንግስትም ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ የበኩሉን ጥረት ማድረግ አለበት ብለዋል።

ለአገር እድገት ወጣቱ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ያሉት ኢንስፔክተር ታደሰ አለማየሁም  ምርጫው ሰላማዊ ፤ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሀዊ እንዲሆን ወጣቱ ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን ሰፊ ስራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

ኮሎኔል ዳንኤል ጉሳ በበኩላቸው ከዚህ በፊት የተካሄዱ ምርጫዎች የራሳቸው ችግር እንደነበሩባቸው አንስተው በመጪው ምርጫ የተሻለ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

ገዢው ፓርቲ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ትክለለኛ መረጃዎች እና ንግግሮችን ለህብረተሰቡ ሊያስተላልፉ ይገባልም ብለዋል፡፡