ከአርባ ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለዞኖች ተሰራጭቷል- ኢንተርፕራይዙ

77

መጋቢት 26/2013 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የምዕራብ ሪጅን ጽህፈት ቤት ከ40 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ የበቆሎ ዘር ለተለያዩ ዞኖች ማሰራጨቱን አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፉፋ ሾሮ ለኢዜአ እንደገለጹት  ለ2013/2014 የምርት ዘመን በልግና መኽር ወቅት እርሻ የሚያገለግል ከ40ሺህ ኩንታል በላይ የበቆሎ ምርጥ ዘር ለዞኖች ተሰራጭቷል ።

ምርጥ ዘሩ የተሰራጨው  ለሐረርጌ፣ ለጉጂ፣ ለቦረና፣ ለምሥራቅ ሸዋ፣ ለምዕራብ አርሲ፣ ለአርሲ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ለጅማ፣ ለኢሉ አባቦር፣ ለቡኖ በደሌና ለአራቱ ወለጋ ዞኖች ነው።

የተሰራጨው ምርጥ ዘር ቢ.ኤች 661፣ 546፣ 547፣ 540ና 140 የተሰኙ የበቆሎ ዝርያዎችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

ምርጥ ዘሩ  ባለፈው አመት በኢንተርፕራይዙ፣ በባለሀብቶችና በገበሬዎች ማሳ በ6 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከተባዛው 97 ሺህ 150 ኩንታል ውስጥ የተሰራጨ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

አሁን ላይ ለምርት ዘመኑ የሚሆን  ቢ.ኤች 661 እና የሌሎችም ምርጥ የበቆሎ ዝርያ ዘር  በበቂ ሁኔታ መኖሩን ያመለከቱት ሥራ አስኪያጁ ከ7ሺህ ኩንታል በላይ የቦሎቄ፣ የአኩሪ አተር፣ የኑግ፣ የሰሊጥ፣ የኦቾሎኒ፣ የዳጉሳና የማሽላ ዘሮችን ለማሰራጨት ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል ።

የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የዘር ብዜትና የማዳበሪያ አቅርቦት ባለሙያ አቶ ቀናቴ ጀቤሣ ከኢንተርፕራይዙ የተላከ 2ሺህ 810 ኩንታል የቢ.ኤች ዝርያ የሆኑ የበቆሎ ምርጥ ዘር ለዞኑ መድረሱን ገልጸዋል።

ምርጥ የቆሎ ዘሩን ለአርሶ አደሮች ለማከፋፈል በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የምሥራቅ ወለጋ ዞን የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የግብርና ሜካናይዜሽንና የግብርና ግብዓት አቅርቦትና አጠቃቀም ባለሙያ አቶ አስፋው አዱላ በበኩላቸው ከኢንተርፕራይዙ የተላከ 6ሺህ 170 ኩንታል የቢ.ኤች ዝርያ የበቆሎ ምርጥ ዘር በዞኑ ለ15 ወረዳዎች  መሰራጨቱን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም