የግድቡ ግንባታ ሰራተኞችና ኃላፊዎች በእሳት የተፈተኑ የልማት አርበኞች ናቸው - ዶክተር አረጋዊ በርሄ

106

መጋቢት 25 ቀን 2013 (ኢዜአ) የቀድሞው የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) መስራች ናቸው። ከዓመታት በኋላ በህወሃት አመራሮችና በእርሳቸው መካከል የሃሳብ ልዩነት በመፈጠሩ ራሳቸውን ከድርጅቱ አገለሉ። ለዓመታት ኑሯቸው ባህር ማዶ አድርገው የአገራቸውን የፖለቲካል ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በንቃት ሲከታተሉ ቆይተዋል።

በአሁኑ ወቅትም የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) መስራችና ሊቀመንበር ናቸው። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገራቸውንና ህዝባቸውን እያገለገሉ ይገኛል ዶክተር አረጋዊ በርሔ።

ዶክተር አረጋዊ የኢትዮጵያዊያን የጋራ አሻራ ያረፈበትን ግድብ የ10 ዓመታት የግንባታ ሂደት አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል። ሙሉ ሃሳባቸው እንደሚከተለው ቀርቧል።

ባለፉት 10 ዓመታት ለግድቡ ክንውን የህዝቡ ተሳትፎና የተገኙ ውጤቶች እንዴት ይገለጻሉ?

ግድቡ ከተጀመረ አስር ዓመት ሆኖታል። ግድቡ በተጀመረ ማግስት የነበረው ህዝባዊ ተሳትፎና ተነሳሽነትም የሚያስደንቅ ነበር። ዋል አደር እያለ ሲመጣ ግን የነበረው ተነሳሽነትና ተሳትፎ ቀንሶ ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበረው የህወሃት-ኢህዴግ በግንባታ ሂደት ላይ ግልጸኝነት የጎደለው አሰራር መዘርጋቱ ዋነኛ ምክንያት ነበር።

በዚህም ግድቡን በታቀደለት አምስትና ስድስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ አልተቻለም። የተሰበሰበው የህዝብና የአገር ሃብት ምዝበራም በግንባታ ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ፈጥሮ ነበር። ከአገራዊ ለውጡ ማግስት ግን የነበሩ ችግሮችን በጥናት በመለየት ግልጽ የሆነ ህዝባዊ ተሳትፎ ተፈጥሮ የግድቡ ግንባታ ላይ የሚያኮራ ለውጥ ታይቷል።

በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያዊያን የጋራ ስለሆነው ግድባቸው በኩራት የሚናገሩበት እና በእውቀት፣ በጉልበትና በገንዘብ አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በግድቡ የውስጥና የውጭ ጫናዎች አሉበት፤ ኢትዮጵያዊያን ግን ጫናዎቹን በሚገባ ለመወጣት እንደፈለጉ የሚያሳይ እድገት ታይቷል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በአምስትና ስድስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እስካሁን መቆየቱ ያደረሰው ተጽእኖስ? በገንዘብ ሲሳላስ?

አዎ!! ብዙ ተጽእኖ አሳድሯል። ዋናው ግን በግንባታ ወጪ ስም ተንሰራፍቶ የነበረው ሙስና እና ብልሹ አሰራር ነበር። ከዓመታት በፊት በነበሩት የስራ ኃላፊዎች ለግድቡ የሚሰበሰበውን ገንዘብ የራሳቸውን ኪስ ለመሙላት ተጠቅመውበታል። የሙያ ብቃት የሌላቸው ኮንትራክተሮች መሳተፍ፣ ሙስና፣ ብልሹ አሰራር እና ጥራት የሌላቸው የግንባታ ጥሬ እቃዎች መቅረብ ለግድቡ ቀጣይነት የሚያሰጉ ዋነኛ ነገሮች ነበሩ።

እነዚህን ነገሮች ለማጥራትም አንድ ከባድ ስራ ነበር። ሰዎችን አስወግዶ ተጠያቂ ማድረግ በራሱ አንድ ስራ ነበር። በጉልበት፣ በገንዘብ፣ በተፈጥሮ ሃብት ሳይቀር በርካታ ጉዳት ደርሷል። ይህ ሁሉ ተግባር ከተከናወነ በኋላ ግን የግድቡ ግንባታ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲቀመጥ ማድረግ ተችሏል። ለዚህም ነው በአሁኑ ወቅት በአስተማማኝ ደረጃና ፍጥነት በታቀደለት ዓላማ እየሄደ ያለው። የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መከናወኑም አንዱ ማሳያ ነው። በቀጣይም ሁለት የኤሌክትሪክ አመንጪ ተርባይኖች ስራ ይጀምራሉ። ስለዚህ ከለውጡ ወዲህ ባለፉት ዓመታት የደረሱትን ኪሳራዎች ለማካካስ እየተሰራ ነው።

ያጋጠሙ ተጽዕኖዎችን ለማስተካከል ምን ዓይነት የመፍትሔ እርምጃዎች ተወሰዱ?

የግድቡን ሁኔታ ማጥናትና መገምገም የመጀመሪያው ስራ ነበር። ከዚያም የአገር ፍቅርና እውቀት ባላቸው መሃንዲሶችና መካኒኮች በጥናት ውጤቱ መሰረት ግምገማ ተካሂዶ የወደፊት አቅጣጫ ማስቀመጥ ተቻለ። በግድቡ ላይ የነበሩ ችግሮች የት የት እንዳሉ በመለየትም ለማወቅ ተቻለ።

ስለታወቀም ችግሮቹን ለመቅረፍ ለውጥ እንዲመጣ ተደረገ፤ ኃላፊነት መውሰድ ያለባቸው ሰዎችም ተይዘው ለፍርድ ቀርበዋል። አንዳንድ የእውቀትና የአቅም ችግር ያለባቸው ኮንትራከተሮችም ተሰርዘው እንዲወጡ ተደርጓል። ከሙሰኞችና ብልሹ አሰራር ጋር ግንኙነት ያላቸውን ጨምሮ ማለት ነው። ይህ ሁሉ ተግባር ተከናውኖ በአሁኑ ወቅት የግድቡን ሂደት ለማስተካከል ድካም የሚጠይቅ ስራ ተሰርቷል።

በአሁኑ ሰዓት የግድቡ አጠቃላይ የግንባታ ሂደት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አሁን አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ አፈፃፀም 79 በመቶ ደርሷል፤ ቀሪው 21 በመቶ ነው። በአሁኑ ወቅትም ግንባታው በሚያኮራና አስተማማኝ ሁኔታ እየተከናወነ ነው። ይህ ግን ቀላል አይደለም። ኢትዮጵያዊያን የጋራ አሻራቸው ያረፈበት ግድብ ዳር እንዲደርስ የሚያጋጥሙ ጫናዎችን ሁሉ በአንድነት መመከትና ማጠናቀቅ ይኖርባቸዋል።

ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ የሚያደርጉት ድጋፍ እንዴት እየሄደ ነው?

ዜጎች ለግድባቸው የሚያደርጉት ድጋፍ በጣም የሚያኮራ ነው። የአድዋን መንፈስ የተላበሰ እንቅስቃሴም እየተደረገ ይገኛል። የአድዋ መንፈስ ምን ማለት ነው? በዘመናዊ መንገድ የታጠቀና የሰለጠነ ወራሪን ኃይል አንድ ሆኖ የማሸነፍ ጥበብ ማለት ነው። ጣሊያን በወቅቱ ሃያል የአውሮፓ መንግስት ነበር፤ ያንን ማሸነፍ ተችሏል። በወቅቱ አሸናፊ የሆነውም የሰለጠነ ሰራዊት ወይም ከነሱ በለጠ መሳሪያ ስለነበረን አይደለም። ኢትዮጵዊያን ከአራቱም አቅጣጫ በአንድነት በመሰለፋቸው ነው።

ግድቡም በዚያ መንፈስ አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ አስችሎታል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ፣ እና በእውቀቱ የሚችለውን ሁሉ በአንድነት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ህጻናት ሳይቀር ከቁርሳቸው እየቀነሱ ለግድባቸው የሚችሉትን ሁሉ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ናቸው።

በአገሪቱ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችም ለግድቡ አስተዋጽኦ ለማድረግ የጋራ ፎረም በመመስረት የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ድጋፍ እያደረጉ ነው። ዩኒቨርሲቲዎች መሰባሰባቸው የግንባታ ስራውን በሳይንሳዊ ዘዴ እንዲታገዝ የሚኖረው አስተዋጽኦ የማይተካ ነው።

አጠቃለይ ኢትዮጵያዊያን ህጻን፣ ወጣት፣ አዛውንት፣ ሴት፣ ወንድ፣ የተማረ ይሁን ያልተማረ ሳይሉ ለግድባቸው ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊያን ግድቡ ተጠናቆ ከነበሩበት የጨለማና ጎስቋላ ኑሮ ወደ ተሻለ የእድገት ደረጃ እንደሚያሻግራቸው መሆኑን ተረድተዋል።

በግንባታ ሂደቱ የዲያስፖራው ማህበረሰብ ተሳትፎ ሁኔታን ቢገልጹልን?

ከዓመታት በፊት ውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ተከፋፈለ ነበር። ግማሹ ለውጥ ፈላጊ ነው ግማሹ ደግሞ የነበረው መንግስት ደጋፊ ነው። ስለዚህ ተባብሮ አይንቀሳቀስም ነበር። ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ግን ከጥቂት "ጯሂ የህወሃት ደጋፊዎች" ውጪ አብዛኛው ውጭ የሚኖር ኢትትዮጵያዊ ለመንግስት ድጋፍን አጠናክሮ በመቀጠል ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያዊያንም የግድቡን መገንባት ፋይዳ በቅጡ ስለሚረዱ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው በመቀጠል ላይ ይገኛሉ። የዳያስፖራው ማህበረሰብም በተለያዩ አገራት ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ጋር በመተባበር ከገንዘብ ድጋፍ እስከ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አይነተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው።

ለግድቡ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል?

ሁሉም ስራዎች በቅንጅት እየተሰሩ ነው። ከዚህ በፊት ውሃ የሚተኛበት የመሬት ጽዳትና ምንጣሮ በሚል በርካታ ሚሊዮን ሃብት ተመዝብሮበታል። በአሁኑ ወቅት ግን ሁሉም ነገር ግልጽና ህጋዊነት በተላበሰ መልኩ እየተሰራ ነው። ስለዚህ በሚቀጥሉት ወራቶች ሁለተኛው ዙር ውሃ ሙሌት የሚተኛበት መሬት ጽዳትና ምንጣሮ ይከናወናል።

ለግድቡ ግንባታ እስካሁን ምን ያህል ገንዘብ ተሰበሰበ?

ግድቡ ከተጀመረበት ጀምሮ ከ15 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ ተሰብስቧል። በዚህ ዓመትም 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር መሰብሰብ ተችሏል። ሚሰበሰበው ገንዘብም በየጊዜው ለግንባታ ስራው እንዲውል እየተደረገ ነው።

ግድቡን ለማጠናቀቅ በመንግስት በኩል ያለው ቁርጠኝነት?

ለግድቡ መሳካት መንግስት ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው፤ ነበርም። አገሪቱ ለውጥ ውስጥ ከገባች ወዲህ መንግስት ግድቡን ለማጠናቀቅ በሙሉ አቅሙ እየሰራ ነው። መንግስት ቁርጠኛ ባይሆን ኖሮ ግድቡ ከነበረበት ውስብስብ ችግር ወጥቶ አሁን ካለበት የሚያኮራ ደረጃ ላይ ባልደረሰ ነበር። እናም መንግስት ለግድቡ ስኬት ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ስራ በማከናወን ያልተቆጠበ ስራ በመስራት ላይ ነው።

በስፍራው የተሰማሩ ሰራተኞችና የስራ ኃላፊዎች ተነሳሽነት ምን ይመስላል?

በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። በስፍራው በግንባታ ሂደት እየተሳተፉ የሚገኙ ሰራተኞችና ስራ ኃላፊዎች በእሳት የተፈተኑ የልማት አርበኞች ናቸው ማለት ይቻላል። በስፋራው ያለውን ሃሩር ተቋቁመውም በሁለት ፈረቃ 24 ሰዓት ሙሉ ሌት ከቀን በስራ ላይ ናቸው። በእውነትም በስፍራው ያሉ ሰራተኞችን እንኮራባቸዋለን። የግድቡ ግንባታ አፈፃፀም አሁን ላይ 79 ከመቶ ደርሶ 10ኛ አመት በደፈነበት ወቅት መድረሳቸውም ኩራት ሊሰማቸው ይገባል።

የግድቡ ግንባታ መች ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል?

ግድቡን በሚቀጥሉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው። የግንባታ ሂደቱም በታሰበው ልክ በተሻለ ፍጥነትና ጥራት እየተከናወነ ይገኛል። ስለዚህ በሚቀጥሉት ዓመታት ውስጥ በተያዘለት ስሌት ይጠናቀቃል።

ግድቡ ሲጠናቀቅ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለፈ የሚሰጠው የኢኮ-ቱሪዝም ፋይዳ ይኖር ይሆን?

ግድቡ ሲጠናቀቅ ለኢኮ-ቱሪዝም ምጣኔ ሃብታዊ መነቃቃቱ ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል። ግድቡ በሚሰራው ሃይቅ ከተለያዩ አገራት ለመዝናናት የሚመጡ አካላት ይኖራሉ። በስፍራውም የሆቴልና ቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲፈጠር ያደርጋል። በዚህም በርካታ ዜጎች የስራ ባለቤት እንዲሆኑ ይደረጋል።

ግድቡ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?

በቅድሚያ ለሁሉም ኢትዮጵያዊን እንኳን ለ10ኛ ዓመት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አደረሳቹህ ማለት እፈልጋለሁ። የግድቡ ግንባታ ሂደት ከነበረበት ችግር ወጥቶ እዚህ በመድረሱ እኔ በግሌ እኮራለሁ፤ ኢትዮጵያዊያንም ሊኮሩ ይገባል። ሁሉም ዜጋ በጉልበቱ፣ በገንዘቡ፣ በእውቀቱና በእጁ እየሰራው ያለ የጋራ አገራዊ ፕሮጀክት ነውና።

አሁን የቀረን 21 በመቶ ግን ከፍተኛ ርብርብ የሚጠይቅ ስለሆነ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን በአንድነት በመመከት በጋራ መቆም ይኖርብናል።

የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?

አገር ቤትም ሆነ ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ግድቡ ከፍጻሜ እንዲደርስ እያደረጉት ላለውና ለሚያደርጉት ያላሳለሰ ድጋፍ ሁሉ ምስጋናዬ ይድረሳቸው። ሁሉም ኢትዮጵዊያን እጅ ለእጅ በመያያዝ የጋራ አሻራቸው ያረፈበት ግድባቸው እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚያደረጉትን የገንዘብ፣ የእውቀትና የጉልበት ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም