የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ በአገራዊ አንድነት ሰላምና የጋራ መግባባት ላይ ማተኮር እንዳለበት ተጠቀመ

124

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2013 /ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ በአገራዊ አንድነት፣ አብሮነት እንዲሁም ሰላምና የጋራ መግባባት ላይ ትኩረት ያደረገ እንዲሆን ተጠየቀ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበር ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ አዘጋገብ ላይ ለጋዜጠኞች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።         

በስልጠናው ላይ ከተለያዩ የመንግስትና የግል መገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ሲሆን ባለሙያዎች በምርጫ ወቅት በመረጃ ላይ የተሰመረተ ዘገባ እንዴት መስራት ይችላሉ? የሚለው ዋነኛ የትኩረት ነጥብ ሆኗል።     

ስልጠናው የመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲ፣ ማስተግበሪያ አዋጅ እንዲሁም የምርጫ አዘጋገብ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ባለሙያዎች የሚሰለጥኑባቸው ርዕሶች ናቸው።   

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የመገናኛ ብዙሃን በኃላፊነት ሊሰሩ የሚገባበት ወቅት ነው።

"አሁን ላይ የአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን አዘጋገብ ግጭቶችን እያባባሰ ነው" ያሉት ሥራ አስፈጻሚው በዚህም የአገሪቷ ፍቅር፣ ሠላምና አንድነት አደጋ ውስጥ እየገባ መሆኑን አንስተዋል። 

ከቀጣዩ ምርጫ ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ዘገባዎች ሥነ ምግባርን ያማከሉ ሊሆኑ እንደሚገባና በስራዎቻችን ህዝቦችን የማቀራረብ ኃላፊነት እንዳለብን መገንዘብ ይገባናል ብለዋል።

"አሁን ላይ የመገናኛ ብዙሃን በአንድ ቀን ውስጥ የሚጣረሱ መረጃዎችን የሚያወጡበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፤በዚህም ምክንያት ህዝቡ ትክክለኛ መረጃ ከማግኘት ይልቅ ወደ መጠራጠርና ወደ ማዘን እየገባ ነው" ብለዋል።    

መገናኛ ብዙሃን ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን ወሳኝ ሚና ያላቸው በመሆኑ በጥንቃቄ ሊሰሩበት እንደሚገባም አክለዋል።  

በተለይም የሚመጡ መረጃዎች ትክክለኛና በእውነታ ላይ መመስረት እንደሚኖርባቸው ጠቁመው ይሄንን ተግባራዊ ለማድረግም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ራሱን የቻለ የመረጃ ማረጋገጫ ክፍል ሊያቋቁሙ እንደሚገባ አመልክተዋል።   

የህግ ባለሙያው አቶ ሰለሞን ጎሹ በበኩላቸው የመገናኛ ብዙሃን ምርጫውን ሙያዊ ነጻነታቸውን በጠበቀ መልኩና በኃላፊነት መዘገብ እንዳለባቸው ተናግረዋል።  

ጋዜጠኛው መብትና ግዴታዉን ጠንቅቆ ካወቀ ስራውን በአግባቡ እንዲያከናውን የሚያግዘው በመሆኑ ባለሙያዎች ራሳቸውን በማብቃት በኩል በትኩረት እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

አሁን ላይ በቴክኖሎጂ የታገዙ ሀሰተኛ ዘገባዎች፣ንግግሮችና ምስሎች እየወጡ በመሆኑ ባለሙያው ጥንቃቄ የታከለበት ስራ ማከናወን እንደሚኖርበትም አሳስበዋል።  

ጋዜጠኞች ከምርጫው ጋር በተያያዘ የወጡ መመሪያዎችና አዋጆችን በሚገባ ማወቅ እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል።  

ለጋዜጠኞች የሚሰጠው ስልጠና ዛሬ የተጀመረ ሲሆን በነገው እለትም ይጠናቀቃል።  

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ማህበር የጋዜጠኛውን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ከስምንት ወራት በፊት የተቋቋመ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም