በመረጃ ልውውጥ ተመራጭና ቀዳሚ ለመሆን እየሰራሁ ነው- ኢትዮቴሌኮም

271

ባህር ዳር መጋቢት 23/2013 ( ኢዜአ) ኢትዮ -ቴሌኮም በመረጃ ልውውጥ ፈጣን፣ ተመራጭና ግንባር ቀደም ኩባንያ ለመሆን አልሞ እየሰራ መሆኑን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ  ፍሬህይወት ታምሩ አስታወቁ።

በኢትዮ ቴሌኮም ሰሜን ምዕራብ ሪጅን 4ኛው ትውልድ ኤል ቲ ኢ የተንቀሳቃሽ እጅ ስልክ ኢንተርኔት አገልግሎትን ዛሬ አስጀምሯል።

ዋና ስራ ስፈፃሚዋ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት ኢትዮ ቴሌኮም የሃገሪቱን የኢኮኖሚ እድገትና የህዝቡን የመረጃ ልውውጥ ፍላጎት መሰረት በማድረግ ሰፋፊ የማስፋፊያ ስራዎችን እያከናወነ ነው።

ባለፉት ዓመታት በተሰሩ  የማስፋፊያ ስራዎች በሃገሪቱ የተንቀሳቃሽ እጅ ስልክ  ተጠቃሚዎች ቁጥር 52 ነጥብ 7 ሚሊዮን መድረሱን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

 የኢንተርኔት ተጠቃሚ ደንበኞችን ቁጥር ደግሞ 24 ነጥብ 4 ሚሊየን  መድረሱን አመልክተዋል።

ቴክኖሎጂው ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች የማስፋፊያ ግንባታዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ጠቅሰው የአገልግሎት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማሻሻል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በኩባንያው በሦስት ዓመት መሪ እቅዱ እድገት፣ ምርታማነት፣ውጤታማነትና ትርፋማነትን ለማረጋገጥ አጽኖት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ጥራትን፣ ተመራጭነትን፣ ቀዳሚነትን አንዲሁም ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ፍጥነትን መሰረት በማድረግ አበረታች ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አክለው የ4ተኛው ትውልድ የኢንተርኔት አገልግሎት ፈጣን የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር በማድረግ የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት መሰረት ተደርጎ የተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በሰሜን ምዕራብ ሪጅን የሚገኙ ባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ቡሬ፣ ዳንግላ፣ አንጅባራና ቻግኒ ከተሞች የሚገኙ ደንበኞች አገልግሎቱን እንደሚያገኙ አብራርተዋል።

ኩባንያው የኢንተርኔት አገልግሎትን በአፍሪካ ሃገራት በተሻለ ደረጃ ለደንበኞች እያቀረበ መሆኑን ጠቅሰው የኢንተርኔት አገልግሎቱ ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጠቀሜታ እንዲውል የአጠቃቀም ባህል መሻሻል እንዳለበት አመልክተዋል።

የ4ኛ ትውልድ ኢንተርኔት አገልግሎት ቀደም ሲል በአዲስ አበባና አዳማ መጀመሩን ጠቅሰው በቀጣይም በሌሎች ከተሞች የማስፋፋት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አስታውቀዋል።

ኩባንያው ቴክኖሎጂውን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግና የዲጅታል ኢኮኖሚ እንዲስፋፋ በቅርቡ ሁለት ሌሎች ኩባንያዎች ወደ አገልግሎት ዘርፉ እንዲገቡ ለማድረግ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆንም ጠቅሰዋል።

የአምበሳ ኢንሹራንስ ባህር ዳር ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ የኔሰው ተመስገን በበኩላቸው ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት የሚያበረታ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ስራዎች ሁሉ በኢንተርኔት ላይ መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው "በተለይም ከዚህ ቀደም በነበረው የኔት ወርክ መጨናነቅ በኢንሹራንሱ የቢዝናስ እንቅስቃሴ ላይ ችግር ይፈጥር ነበር " ብለዋል።

ኩባንያው አሁን ላይ የደንበኞችን ችግር ለመፍታት ያደረገው የ4ኛው ትውልድ ኢንተርኔት አገልግሎት ችግሩን ሙሉ በሙሉ ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው አመላክተዋል።

"ቀደም ሲል የኢንተርኔትም ሆነ የተንቀሳቃሽ ተእጅ ስልክ  ግንኙነት የመቆራረጥ ችግር ነበረ" ያሉት ደግሞ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ዘሪሁን ንጉስ ናቸው።

"ኩባንያው የደንበኞችን ቅሬታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ማሻሻያ ማድረጉ የተሻለ የንግድ ስራዎችን ለመስራት ያግዛል" ብለዋል።

ኩባንያው የጊዜው ፍጥነትና የቴክኖሎጂ እድገትን ባገናዘበ መልኩ   የሚመጡ ቴክኖሎጂዎችን ፈጥኖ ሊያቀርብ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በስነ ስርአቱ ላይ የአማራ ክልል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅ ሰሙ ማሞና ሌሎች የፌደራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች እነዲሁም የኩባንያው ደንበኞች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም