አገር አቀፉ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲከናወን መንግስት ዝግጅት ማድረጉ ተገለጸ

80

መጋቢት 22/2013(ኢዜአ) ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን መንግስት አስፈላጊውን ዝግጀት አድርጓል ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ፡፡

ለዚሁ ስራ የሚያግዝ አገር አቀፍ የምርጫ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱንም አማካሪው ጠቁመዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ይህን ያሉት ዛሬ በአዲስ ወግ የውይይት መድረክ ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

መንግስት መራጮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ታዛቢዎችና የመገናኛ ብዙሃን ደህንነታቸው ተጠብቆ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪ የምርጫ ቁሳቁሶች ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እንዲጓጓዙ እጀባ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የምርጫው ሂደት ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅም የፌዴራል ፖሊስ ፣ ብሄራዊ ደህንነትን እና ሌሎች የጸጥታ ተቋማትን ያካተተ ብሄራዊ የምርጫ ኮሚቴ ተቋቁሞ የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮው ምርጫ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ከተካሄዱ ምርጫዎች በተሻለ መልኩ እንዲከናወን ሁሉም አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም አቶ ገዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም