ዳያስፖራው ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ 50 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ አደረገ... የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ

91

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2013(ኢዜአ) ዳያስፖራው ባለፉት 10 ዓመታት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 50 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እንደሚናገሩት ዳያስፖራው ኢትዮጵያ በራሷ ወጪ ለምትገነባው ግድብ በቦንድ ግዢና በስጦታ እየደገፈ ነው።

የግድቡ መሰረት ድንጋይ በተጣለበት ዓመት ከ13 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉንና ይህም እስካሁን ዳያስፖራው ለግድቡ ግንባታ ካደረገው ድጋፍ ከፍተኛው መሆኑን ገልጸው፤ ከ2005 እስከ 2009 ይደረግ የነበረው ድጋፍ ጥሩ የሚባል እንደነበረም ያስታውሳሉ።

እስከ 2012 ባለው ጊዜ ድጋፉ መቀዛቀዝ እንደታየበትና በሶስት ዓመታት የተደረገው ድጋፍ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በታች ነበርም ብለዋል።

መንግሥት የግድቡን ግንባታ ለማፋጠን የወሰዳቸው እርምጃዎችና የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት ዳያስፖራው ላይ ከፍተኛ መነቃቃት እንደፈጠረ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ዳያስፖራው ለግድቡ ግንባታ ባለፉት 10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ 50 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ በቦንድ ግዢና ስጦታ ማድረጉን ነው ወይዘሮ ሰላማዊት የገለጹት።

ባለፈው ዓመት የተካሄደ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት የፈጠረው መነቃቃት በ2013 በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል።

በዚህ በጀት ዓመት እስካሁን የተደረገው ድጋፍ ባለፈው በጀት ዓመት ከተሰበሰበው ገንዘብ ከ50 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።

ኤጀንሲው በዳያስፖራው የተፈጠረውን መነቃቃት በመጠቀም የተሻለ ሀብት ለማሰባሰብ የሚያስችል እቅድ አዘጋጅቶ እየተገበረ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ የሀብት አሰባሳቢ ቡድን ተዋቅሮ ሥራ መጀመሩንም ዋና ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።

ዳያስፖራው ድጋፍ የሚያደርግባቸው አማራጮችን የማስፋት ተግባር እየተከናወነ ይገኛልም ነው ያሉት።

በተለይም ዳያስፖራው ቦንድ መግዛት በማይችልባቸው አገሮች ኢትዮጵያዊያን በሚገኙበት ባንኮች ገንዘባቸውን እንዲልኩ ለማድረግ ሁኔታ ማመቻቸታቸውን አስረድተዋል።

ዳያስፖራው ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ በፍትሐዊነት የመጠቀም መብቷን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እያስረዳ መሆኑን ገልጸው፤

በተለይም ግብጽና ሱዳን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያሰራጯቸውን ሀሰተኛ መረጃዎችን የማጋለጥና ትክክለኛ መረጃዎችን የመስጠት ተግባር እያከናወኑ ናቸው ብለዋል።

በዚህም መልካም ጅምሮችና ሚዛናዊ ምልከታዎች በማየት ለዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ማሳወቅ በተደራጀ መልኩ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፉን እንዲያጠናክርም ወይዘሮ ሰላማዊት ጥሪ አቅርበዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ዳያስፖራው ማህበረሰብ ለግድቡ 200 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስካሁን ከ15 ነጥብ 1 ቢሊዮን በላይ መሰብሰቡን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት መረጃ ያሳያል።

በ2013 በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁን ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡም ታውቋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም መቀመጡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም