የሴቶችና ህጻናት ጥቃትን ለመቀነስ የፍትህ አካላት በትኩረት መስራት አለባቸው - ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር

144

ባህርዳር፣  መጋቢት 21/2013(ኢዜአ)  በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለመቀነስ የፍትህ አካላት የተጣለባቸውን ሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው የኤፌዴሪ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆም የሚያስችሉ ህጎችና መመሪያዎችን ለባለድርሻ አካላት የሚያስተዋውቅ መድረክ በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በሚኒስቴሩ የህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አማካሪ ወይዘሮ ዘቢደር ቦጋለ በመድረኩ ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ድንጋጌን ተቀብላ ያጸደቀች አገር ናት።

ከዚህ በተጨማሪም ከህገ-መንግስቱ ጀምሮ እስከ ቤተሰብ ህጉ ድረስ ለሴቶችና ህጻናት ልዩ ትኩረት የሰጡ አዋጆች፣ መመሪያዎችና ደንቦችን በማጽደቅ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በቤተሰብ ሞት፣ ፍች፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በሚደርስ መፈናቀል፣ ሞትና የአካል መጉደል ግንባር ቀደም ተጠቂ የሚሆኑት ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውን አስረድተዋል።

“ይህን ችግር ለማቃለልም የፍትህ አካላት የወጡ ህጎችን ተጠቅመው ለሴቶችና ህጻናት መብት መከበር ዘብ እንዲቆሙ በመርህ ደረጃ ቢቀመጥም በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ አልመጣም” ብለዋል።

ሚኒስቴሩም መድረክ በማዘጋጀትና በሚዲያ በመጠቀም ለህብረተሰቡና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት በችግሩ አሳሳቢነትና መፍትሄው ላይ ያተኮረ ተከታታይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ሰላማዊት አለማየሁ በበኩላቸው እንደተናገሩት የሴቶችና ህጻናት ጥቃት ከኮሮና መስፋፋትና አሁን እየተከሰተ ካለው የዕርስ በዕርስ ግጭት ጋር ተያይዞ እየተስፋፋ መጥቷል።

“አብዛኛው ጥቃት የሚፈጸመው በቅርብ ዘመድና አብሮ በሚኖር ሰው በመሆኑ መረጃ በወቅቱና በአግባቡ አግኝቶ ርምጃ ለመውሰድ አስቸጋሪ መሆኑ የችግሩን አሳሳቢነት ያጎላዋል” ብለዋል።

“መረጃው ተገኝቶ ወደ ህግ የሚመጡትም ቢሆን በመርማሪ ፖሊሲዎችና ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተው ባለመያዝና የሌሎች አካላት ትብብር ማነስ ምክንያት ተገቢውን ፍትህ እያገኙ አይደለም”ብለዋል።

ቢሮውም በክልሉ በስፋት የሚፈጸመውን የልጅነት ጋብቻ፣ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትና የህጻናት የጉልበት ብዝበዛ ለመግታት የሚያስችል ፍኖተ ካርታ አውጥቶ እየተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ለዚህም ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችና ህጻናት ከለላ የሚያገኝባቸው ማዕከላት በባህርዳርና በደሴ በማቋቋም ነጻ መጠለያ፣ ምግብ፣ ህክምናና ፍትህ እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህጻናት ፍትህ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ልዑለስላሴ ሊበን ባቀረቡት ጽሁፍ እንዳመላከቱት የህጻናት መብቶች ያለማንኛው መድሎ መከበርና መረጋገጥ እንዳለበት በዓለም አቀፍም ሆነ በአገራችን ህጎች ተደንግጓል።

“በዓለም የህጻናት ኮንቬንሽን፣ በህገ-መንግስቱና በቤተሰብ ህጉ በማንኛውም ርምጃ በሚወሰድበትና ውሳኔ በሚሰጥበት ጉዳይ ላይ ቅድሚያ ለህጻናት መብት መጠበቅና ደህንነት መከበር መስጠትያስፈልጋል”ብለዋል።

“ለዚህም በየደረጃው የሚገኙ የፍትህ ተቋማት ህጉን በአግባቡ በመተርጎም ለተጎጂዎች ወገንተኛነታቸውን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት በመስራት ለውጥ ማምጣት አለባቸው” ብለዋል።

ለተከታታይ ሶስት ቀናት በሚካሄደው መድረክም በፍትህ ስርዓቱ የህጻናትና ሴቶች አያያዝ፣ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ ያተኮሩ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የሚካሄድባቸው መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም