በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ የተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት ዘላቂ እንዲሆን ነዋሪዎች ከፀጥታ ሃይሉ ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገለጹ

65

መጋቢት 15፤2013 (ኢዜአ) በሽሬ እንዳስላሴ ከተማና አካባቢው የተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት ዘላቂ እንዲሆን ነዋሪዎች ከፀጥታ ሃይሉ ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገለጹ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት በህወሓት ጁንታ ላይ የህግ ማስከበር እርምጃ ከተወሰደ ወዲህ ከተማዋ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተመልሳለች፡፡የህወሓት ጁንታ ታጣቂ ሃይል በሰሜን ዕዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ባደረሰው ጥቃት መንግስት የህግ ማስከበር እርምጃ መውሰዱ ይታወሳል።

በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ከተካሄደባቸው አካባቢዎች የሰሜን ምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች ሽሬ ከተማ አንዷ ስትሆን አሁን ላይ በከተማዋ ነዋሪዎች በሰላም የየእለት ስራቸውን በማከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።የከተማዋ ነዋሪዎች ከአገር መከላከያ ሰራዊትና ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመሆን በአካባቢው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር መስራታቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢው አልፎ አልፎ የስርቆትና ዘረፋ ወንጀል ስለሚስተዋል ለጋራ ደህንነታቸው ከፀጥታ ሃይሉ ጋር አብረው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።ከነዋሪዎች መካከል ወጣት ነስረዲን ከድር እንደሚለው በሽሬ ከተማና አካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲኖር በተለይ ወጣቶች ከጸጥታ አካላትና ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር በቅንጅት እየሰሩ ነው።

የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሃላፊ ዶክተር ቴድሮስ አረጋይ በበኩላቸው የዞኑን ሰላም ለማስጠበቅ ከህብረተሰቡና ከጸጥታ አካላት ጋር በጋራ እየሰራን ነው ብለዋል።ከተማዋ ጊዜያዊ አስተዳደር የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማደራጀት ሰላምና ጸጥታ የማስፈን ስራ በማከናወኑ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም