ወጣቶች የምርጫ ስነ-ምግባርን በማወቅና በማክበር ለምርጫው ሂደት ሠላማዊነት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

72

  አዲስ አበባ (ኢዜአ) መጋቢት 14/2013 ወጣቶች የምርጫ ስነ-ምግባርን በማወቅና በማክበር ለምርጫው ሂደት ሠላማዊነት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።

የአዲስ አበባ አስተዳደር የወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጋር በመተባበር በምርጫ ሕግና ስነ-ምግባር ላይ የአንድ ቀን ስልጠና ሰጥቷል።

ስልጠናው በምርጫ ሕግ እና የስነ-ምግባር አዋጅ ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ ከ300 በላይ የሚሆኑ በተለያዩ አደረጃጀት ውስጥ የሚሰሩ አካላት ተሳትፈውበታል።

በቢሮው የወጣቶች ግንዛቤ ተሳትፎና ማካተት ዳይሬክተር አቶ ጤናዬ ታምሩ ስልጠናው ወጣቶች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ግንዘቤ እንዲኖራቸው መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የወጣቶችን የምርጫ ተሳትፎ ማሳደግም የስልጠናው ሌላው ዓላማ ነው።

ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሠላማዊ እንዲሆን የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሚና ከፍተኛ ቢሆንም ወጣቶች ደግሞ የበለጠ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በመሆኑም ስልጠናው ወጣቶች ምርጫውን በሚመለከት ያላቸውን እውቀት በማሳደግ የበኩላቸውን እንዲወጡ ያግዛል ብለዋል።

ዳይሬክተሩ ወጣቶች ምክንያታዊ አስተሳሰብን ባህሪያቸው እንዲያደርጉም መክረዋል።

በአዲስ አበባ አስተዳደር ዐቃቢ ሕግ ቢሮ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ባለሙያ ሩቂያ ተፈራ በበኩላቸው ስልጠናው ወጣቶች በምርጫ ላይ ያላቸውን መብቶችና ግዴታዎች እንዲለዩ ያስችላቸዋል ብለዋል።

ለምርጫው ሠላማዊነት የምርጫ ሕግና ስነ-ምግባርን ማወቅና ማክበር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ወጣቶች ስሜታዊነትን በማስወገድ አላስፈላጊ ድርጊቶች ውስጥ መሳተፈ እንደሌለባቸው አሳስበዋል።

በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች የሚለቀቁ መረጃዎችን በሰከነ መንፈስ መመርመር እንዲሁም የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን  በውይይት መፍታት እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በምርጫ ሕጉ ላይ የሚሰጠው ስልጠና ከወጣቶች በተጨማሪ ለሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችም ተደራሽ እንዲሆን ጠይቀዋል።

በስልጠናው ስለ ምርጫ ስነ-ምግባር ግንዛቤ ማግኘታቸውን ጠቁመው፤ በቀጣይም በስልጠናው መሰረት በምርጫው ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወጣቶች ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በቅድመ እና ድህረ ምርጫ አላስፈላጊ ሁከትና ግርግር የሚፈጥሩ አካላትን መከላከል እንዳለባቸውም ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም