"የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገው 'በትዊተር' የሀሰት ዘመቻ የሚፈጥርለትን ሳይሆን በተግባር የሚደግፈውን ነው" - ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ

226

መጋቢት 14 / 2013 (ኢዜአ) የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገው 'በትዊተር' የሀሰት ዘመቻ የሚፈጥርለትን ሳይሆን በተግባር የሚደግፈውን ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በትግራይ ክልል እየተከናወነ ያለውን የመልሶ ማቋቋም ስራ አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው።

እስካሁን ባለው ሂደት መንግስት የትግራይ ክልልን መልሶ ለማቋቋም 40 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን ተናግረዋል።

መንግስት 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ለሚሆኑ በችግር ውስጥ ለሚገኙ የክልሉ ነዋሪዎች ድጋፍ ማድረጉንም ነው የገለጹት።

በውጭ የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጅ ዳያስፖራዎችና ባለሃብቶች ገንዘብ እያዋጡ የሀሰት ዘመቻ ከሚፈጥሩ ይልቅ ሕዝባቸውን በሚፈልጉት አግባብ መደገፍ እንዳለባቸውም አውስተዋል።

"የትግራይ ክልል ነዋሪዎች የሚፈልጉት 'የትዊተር' የሀሰት ዘመቻ ሳይሆን ተጨባጭ ድጋፍ ነው" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የትግራይ ሕዝብና ሌሎች ክልሎች በትግራይ ክልል የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳዳር እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።

የጁንታው ሃይል በሕግ ማስከበር ዘመቻው ላይመለስ ተበትኗል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተበታተነው ሃይል አልፎ አልፎ በመሰረተ ልማቶች ላይ ችግር የመፍጠር ሙከራ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የፌዴራል የጸጥታ መዋቅር ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳዳር ጋር በመቀናጀት የክልሉን ሠላም ሙሉ ለሙሉ ለመመለስና ቀሪ ወንጀለኞችን የማደን ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም ነው የጠቀሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም