ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ አፍሪካ ለዓለም ሰላም መስፈን የድርሻዋን እየተወጣች መሆኑን ገልጹ

71

መጋቢት 9 / 2013 (ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አፍሪካ ለዓለም ሰላም መስፈን የድርሻዋን እየተወጣች መሆኑን ገልጹ።

በ986ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በአፍሪካ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ዙሪያ ዛሬ ባደረገው የሚኒስትሮች የበይነ መረብ ውይይት ላይ የተሳተፉት አቶ ደመቀ፤ በተለያዩ አገራት በሰላም ማስከበር ግዳጅ ላይ ሆነው የህይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ክብር እንዳላቸው ተናግረዋል።

በዓለም ሰላምና ጸጥታ የማስፈን ዓላማ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ የባለብዙ ወገን መድረኮች መመስረት በምክንያትነት እንደሚጠቀስ በንግግራቸው አውስተዋል።

የሰላም አስከባሪ ኃይል ያሰማሩ አገራት እስከሕይወት መስዕዋዕትነት ድረስ ዋጋ እየከፈሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ አፍሪካም ለዓለም ሰላም መስፈን የድርሻዋን እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል።

ለሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የሚመደበው የፋይናንስና የሎጀስቲክ አቅርቦት መቀነስ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው ስራቸውን እንዲያከናውኑ ያስገደደ መሆኑን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅትም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘም ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚስፈልግ አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ካለው ተጨባጭ ተሞክሮ አኳያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ዙሪያ በሚወጡ ፖሊሲዎችና እቅዶች ወቅት ተሳታፊ ማድረግ ጠቃሚ እንደሆነ አስረድተዋል።

በተሻለ ብቃትና ቅልጥፍና ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ተሳታፊ አገራት መካከል የተሻለ ቅንጅት ማድረግ አስፈላጊ ስለመሆኑ ገልጸው፤ ለአቅም ግንባታ ተግባራት ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ሴቶች ያላቸውን ልዩ ሚና በመጥቀስ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት ማከናወን እንደሚያስፈለግ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመጨመረሻም የአፍሪካ ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ያለባቸውን ተግዳሮቶችን ለመፍታት አፍሪካዊያን የጋራ አቋም በመያዝ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አጽንዖት ሰጥተው መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም