የህወሃት ቡድን ኢትዮጵያዊያንን በዘርና በሃይማኖት በማቧደን በዜጎች መካከል ልዩነት ፈጥሯል-ሜጀር ጀነራል ጌታቸው ገዳሙ

82

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7/2013(ኢዜአ) ከዚህ ቀደም ከፋፋዩ የህወሃት ቡድን ፋሽስት-ጣሊያን የነደፈውን ካርታ በመጠቀም ኢትዮጵያዊያንን በዘርና በሃይማኖት በማቧደን በዜጎች መካከል ልዩነት መፍጠሩንና የሰራዊቱን ክብር ዝቅ አድርጎታል ሲሉ የቀድሞው የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንን ሜጀር ጀነራል ጌታቸው ገዳሙ ገለጹ።

የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ለሚቀላቀሉ የሰራዊት አባላትና ቤተሰቦቻቸው ተገቢው ክብር፣ እንክብካቤና ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

ሜጀር ጀነራል ጌታቸው ገዳሙ ለኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው ሉዓላዊነትና ነፃነት በአንድነት ለዘመናት ታግለዋል።

ለእናት ሀገራቸው ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ጀግኖችን በክብር ከመዘከር ይልቅ በጠላትነት ፈርጆ እንዲታሰሩ፣ እንዲሰደዱና ጠብቀው ባቆዩዋት ሀገር ባይተዋር እንዲሆኑ ማድረጉንም ነው የገለጹት።

መንግስት ህገ መንግስቱን ከማሻሻል ጀምሮ በወጣቶች ዘንድ ልዩነት የሚፈጥሩ ነገሮችን በማስወገድ የአንድነትና የትብብር መንፈስ እንዲፈጠር ማድረግ አለበትም ብለዋል።

ሜጀር ጀነራል ጌታቸው እንደሚሉት ህወሃት የቀድሞ የሰራዊት አባላትን ክብር ዝቅ አድርጎ ከማዋረዱም በላይ ባለው አፍቅሮተ ንዋይ ምክንያት የሰራዊቱን ገንዘብ ቀምቶ ለከፋ ችግር ዳርጓቸው መቆየቱን አንስተዋል።

በቀጣይ ወደ መከላከያ ሰራዊቱ የሚቀላቀሉ ወጣቶች ተገቢውን ክብርና እንክብካቤ የሚያገኙበት ስርዓት መኖሩን በተግባር ማሳየት ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜጎት ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ / ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ፤ ወጣቶች የሀገር ሉዓላዊት ከፖለቲካ አስተሳሰብ የሚለይ መሆኑን ማወቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የመከላከያ ሰራዊት አባላት ዓለም አቀፍ የሚሊታሪ ደረጃን በጠበቀ መንገድ መብታቸውና ጥቅማቸው ሊከበርላቸው ይገባልም ብለዋል።

ይህን በማድረግም ለሀገራቸው ሉዓላዊነት ዘብ የሚቆሙ ወጣቶችን መፍጠር ይቻላል በማለትም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም