ድርጅቶቹ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የስራ ስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ

57
ሀረር ሐምሌ 21/2010 በሐረሪ ክልል በህዝቡ ዘንድ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ መዘጋጀታቸውን ክልሉን የሚመሩት የሐረሪ ብሔራዊ ሊግና ኦህዴድ/ኢህአዴግ አስታወቁ። ድርጅቶቹም ህዝቡ ሲያነሳቸው የቆዩ የመብት፣ የፍትሃዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለማረጋገጥ ትናንት የስራ ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል። በሐረሪ ክልል ኦህዴድ ሰብሳቢ አቶ ገቢሳ ተስፋዬ ከሐብሊ ጋር ሰነዱን ከተፈራረሙ በኋላ  እንደተናገሩት ሰነዱ የህዝቡን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ሰብሳቢው እንዳሉት ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት ግልጽነት የሌላቸው ሹመቶች በማስቀረት የህዝቡን ጥያቄ የሚመልሱ ብቃት ያለውና ሁሉንም ህብረተሰብ በእኩልነት የሚያገለግል አመራር ይመደባል። ስምምነቱ በአሁኑ ወቅት በክልሉ በቄሮ  ሽፋን  የህግ የበላይነት እንዳይከበርና  አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን በጋራ ለመከላከልና ለመስራት ያግዛል። አሁን የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠልና የህብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታት ከድርጅቶቹ በተጨማሪ ህብረተሰቡና ወጣቱ የበኩሉን እንዲወጣም አቶ ገቢሳ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ ሊቀመንበር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው ሰነዱ በክልሉ አመራሮች መካከል የነበረውን ያለመተማመንና ጥርጣሬን በማስወገድ የህዝቡን ጥያቄ በጋራ ለመመለስ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር የክልሉ ነዋሪ ለዘመናት ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር እሴትን ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ ያስችሏል፤ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ይረዳል" ብለዋል። በጸጥታ ኃይሎች የሚታዩ የክህሎት፣ ብቃትና አመለካከት ክፍተቶችን ለማስተካከል እንዲሁም የተቋማትን ክፍተቶችና አድሏዊ አሰራሮችን ስርዓት ለማሲያዝ ማሻሻያ እንደሚደረግ ከስምምነት ላይ ተደርሷል። "ከመንገድ፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃና ሌሎች ከመሰረተ ልማት እንዲሁም ከወጣቱ የስራ እድል ፈጠራ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ለመመለስ በተያዘው በጀት ዓመት በትኩረት ይሰራል "ብለዋል ሊቀመንበሩ። ከህብረተሰቡ ጋር በስፋት በመወያየትም የህዝቡን ቅሬታ በቅደም ተከተል እንደሚፈታ ገልጸው፤ ለዚህም ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደረግ ጠይቀዋል። የሁለቱ ድርጅቶች አመራሮች የስምምነቱን ሰነድ በተፈራረሙበት ወቅት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል። በሐረሪ ክልል ምክር ቤት ሐብሊና ኦህዴድ እያንዳንዳቸው እኩል18 ወንበር እንዳላቸው ታውቋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም