ኢዜማ “የፀጥታ ችግር ባለባቸው ጣቢያዎች የሚወዳደሩልኝ ዕጩዎች በማዕከል ይመዝግቡልኝ” አለ

2343

 አዲስ አበባ መጋቢት 3/2013 የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ምርጫ ቦርድ የፀጥታ ችግር ባለባቸው ጣቢያዎች በቂ የመመዝገቢያ ጊዜ ባለመሰጠቱ ዕጩዎቼ በማዕከል ይመዝግቡልኝ ሲል ጠየቀ።

ኢዜማ በኢትዮጵያ ጉዳይ የውጭ ጣልቃ ገብነትንም አውግዟል።

ኢዜማ ይህን ያለው ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ነው።

ፓርቲው በመግለጫው መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲሰራም ጠይቋል።

በዘንድሮ አገራዊ ምርጫ ከትግራይ ክልል በስተቀር በዘጠኝ ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ለመወዳደር 1 ሺህ 385 እጩዎችን ማቅረቡንም ነው የገለጸው።

ነገር ግን በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አንዳንድ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት እጩዎቼን ማቅረብ አልቻልኩም ብሏል።

በእጩዎች ምዝገባ ሂደት ወቅት የምርጫ ቦርድ የወረዳ ቢሮዎችን በግዜ ሰሌዳ አለመክፈት፣ ከህግ ደንብና መመሪያ ውጪ እንዲሟሉ የሚጠየቁ ጥያቄዎች እንዲሁም የእጩ መዝጋቢዎች አቅምና ብቃት ውስንነት በምርጫ ቦርድ በኩል ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውን ዘርዝሯል።

በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት እጩዎችን ለማስመዝገብ ያልተቻለበት ሁኔታ መኖሩንም ጠቁሟል።

በተጨማሪ በአንዳንድ አከባቢዎች የፓርቲው እጩዎች ከተመዘገቡ በኋላ ራሳቸውን ከምርጫ እንዲያገሉ ማስፈራራት ደርሶባቸዋል ሲልም ቅሬታ አቅርቧል።

እስርና ድብደባ የደረሰባቸው እጩዎች እንዳሉም ጠቁሟል።

በመሆኑም መንግስት የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ሰላምና ደህንነትን እንዲያሰፍን ፓርቲው ጠይቋል።

የምርጫ ቦርድ የፀጥታ ችግር ያለባቸውን ቦታዎች በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በቂ የመመዝገቢያ ጊዜ አለመስጠቱን ጠቅሶ፤  ቦርዱ በተጠቀሱት አካባቢዎች የሚወዳደሩ እጩዎችን በማዕከል እንዲመዘገብለት ጠይቋል።

በሌላ በኩል ፓርቲው የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚያደርጉትን ጥረት ኢዜማ በጽኑ እንደሚያወግዝ አረጋግጧል።

ድርጊቱ የአንድን አገር ሉዓላዊነት መድፈር መሆኑንም ነው ያስታወቀው።

ኢትዮጵያዊነት በዛቻና ማስፈራሪያ የሚንበረከክ ማንነት አይደለም በማለትም ኢዜማ አቋሙን አንጸርቋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባ መጠናቀቁን የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በትላንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ ማሳወቁ ይታወሳል።

የዕጩዎች ምዝገባው በሁለት ዙሮች መካሄዱንና ሂደቱም ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁን ነው የገለፁት።

በዚህም መሰረት በመጀመሪያው ዙር ማለትም ከየካቲት 8 እስከ 21 ቀን 2013 በነበረው የምዝገባ ሂደት በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በሐረሪ፣ በቤኒሻንጉል፣ በጋምቤላና በኦሮሚያ ክልሎች ዕጩዎች ተመዝግበዋል።

ከየካቲት15 እስከ 26 ቀን 2013 በተካሄደው የሁለተኛው ዙር ምዝገባም በአማራ፣ በሱማሌ፣ በአፋር፣ በደቡብና በሲዳማ ክልሎች መካሄዱን አብራርተዋል።

ቦርዱ በምዝገባ ሂደቱ አቤቱታ ያቀረቡ ፓርቲዎችን ለዚሁ ተብሎ በተቋቋመው ዴስክ አማካኝነት ተቀብሎ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ቅሬታቸው እንዲፈታ ማድረጉንም መግለፃቸው ይታወሳል።