ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎታቸውን በመጪው ምርጫ ሊደግሙት ይገባል

60

አዲስ አበባ ፣መጋቢት 02/2013 (ኢዜአ) ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያሳዩትን ተነሳሽነት መጪው ምርጫ ሠላማዊ እንዲሆን በማገዝም ሊደግሙት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ "በጎ ፈቃደኝነት ለማኅበራዊ መስተጋብርና ለሠላም" በሚል መርሃ ግብር ከወጣቶች ጋር ተወያይቷል፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ እንዳሉት ባለፉት ስድስት ወራት በከተማዋ በቁሳቁስና በገንዘብ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው እገዛዎችና ስራዎች በወጣቶች ተከናውነዋል፡፡

የበጎ አገልግሎት ተግባራቱ ከከተማዋ ባለፈ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን መሰረት በማድረግ መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

በጎ ፈቃደኞቹ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በሠላም እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱም ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በበኩላቸው መጪው አገራዊ ምርጫ በሠላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡

ወጣት ሀብተሚካኤል ተስፋዬ ከዚህ በፊት በከተማዋ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ማገልገሉን ጠቅሶ አሁንም አገራዊው ምርጫ ሠላማዊ እንዲሆን ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ የመስጠት ስራ እንደሚሰራ ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ የአድዋን ድል ተከትሎ ለመላው አፍሪካዊያንና ለጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት መሆኗን በማንሳት በቀጣይም ዴሞክራሲያዊና ሠላማዊ ምርጫ በማካሄድ አርዓያነታችንን መድገም ይገባናል ብሏል፡፡

የኮሮናቫይረስና የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ከመደገፍ አንጻር በተለያዩ ስራዎች መሳተፏን የገለጸችው ደግሞ ወጣት ገነት ደመቀ ነች፡፡

ወጣቷ በቀጣይም በተለይም ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በሠላም እንዲጠናቀቅ ለወጣቶች ግንዛቤ ከመስጠት ጀምሮ አባላቱ ለስራቸው የሚያግዟቸውን ውይይቶች ማካሄድ መጀመራቸውን ገልፃለች፡፡

ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሳተፉ ለማድረግ በሌላ በኩል በውይይት የሚያምን ወጣት ለመፍጠር እየሰሩ መሆኑን ተናግራለች፡፡

ወጣት ጥላሁን ወንድሙ በበኩሉ አገሪቷን ካለችበት ድህነት ማውጣት የሚቻለው ሁሉም ተባብሮና ተከባብሮ መስራት ሲችል በመሆኑ ለዚህ ስኬታማነት የድርሻውን በማበርከት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

ሁሉም ዜጋ በተለይም ወጣቱ መጪው አገራዊ ምርጫ በሠላም እንዲጠናቀቅ ከማድረግ አንጻር የድርሻውን ኃላፊነት እንዲወጣ ጠይቋል፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር አገራዊ ምርጫው ሠላማዊና ፍትሃዊ እንዲሆን ከ3 ሺህ በላይ ወጣቶችን በበጎ ፈቃደኝነት ለማሰማራት በዝግጅት ላይ መሆኑን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም