ባለ ጥቁር ነጥቡ “ጥቁር መጋረጃ”…

137
እንግዳ መላኩ/ኢዜአ/:-   ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በተባበረ ክንዳቸው በቀጠናው አስፈሪ የነበረውንና ግዙፉን የአምባገነንነት ተራራ ለመናድ አብረው ቆስለዋል፤ አብረው ደምተዋል፤ ምትክ አልባ ህይወታቸውንም አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ በየጦር አውድማው አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው መላ ዓለምን ያስደመመ ድል ተጎናጽፈዋል፡፡ ድሉን ተከትሎም ኤርትራ በህዝቦቿ ፍላጎት ግንቦት 16 ቀን 1985 ዓ.ም ራሷን የቻለች ሀገር ሆናለች፡፡ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በስጋ የተዛመዱ፣ በቋንቋና ባህል የተሳሰሩ እንደመሆናቸው መጠን ለቀናት እንኳን መለያየት ሳይኖርባቸውና ሳይገባቸው ሁለት አስርት ዓመታትን በጥቁር መጋረጃ መከለላቸው ግን ከባድ ፈተና ሆኖባቸው ቆይቷል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የተጎናጸፉትን ድል በቅጡ ሳያጣጥሙ በሀገራቱ መካከል የተፈጠረው የድንበር ይገባኛል ውዝግብ ተገቢ ያልሆነ ደም ወደ አፋሰሰ ጦርነት በማምራቱ ነው፡፡ በዚሁ ሳቢያ ከሁለቱም ወገን የወደመው ሀብት ንብረት፣ የተፈናቀለው ህዝብ ቁጥርም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ማዶ ለማዶ እየተያዩና እየተነፋፈቁ ሁለት አስርት ዓመታትን በጥቁር መጋረጃ ተከልለው እንዲሻገሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ረዳኢ ገብረ በቅርቡ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያረጋገጡትም ይኼንኑ ነው፡፡ ባለሙያው እንዳብራሩት ልጅ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰርጓ እየተደገሰ ኤረትራ ውስጥ ያለ አባት ወይም እናት የልጃቸውን ሰርግ መታደም አይችሉም ነበር፡፡ በሀዘንም እንዲሁ ነው፡፡ ከማህበራዊ ግንኙነቱ መሻከር ባሻገርም በተለይ በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ ምንም አይነት ልማት ሳይከናወን ወታደራዊ እንቅስቃሴው ብቻ ጎልቶ መቆየቱንም በቁጭት ያስታውሱታል፡፡ ኤርትራ የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታትና የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት /ኢጋድ/ አባል ነች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአረብ ሊግ ውስጥም በታዛቢነት ትሳተፋለች፡፡ ሀገረ ኤርትራ ከሶስት አስርት ዓመታት ትግል በኋላ በህዝቦቿ ፈቃድና ፍላጎት ራሷን የቻለች ሀገር ትሁን እንጂ ከጎረቤቶቿም ሆነ ከሌላው ዓለም ጋር የነበራት ግንኙነት ከዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ ለአብነት ያህልም ከታህሳስ 5-7 ቀን 1988 ዓ.ም በሀኒሽ ደሴቶች ይገባኛል ጥያቄ ከየመን ጋር ጦርነት አካሂዳለች፡፡ ከሚያዝያ 28/1990 - ሰኔ 11/1992 ዓ.ም ደግሞ በድንበር ይገባኛል ጥያቄ ከኢትዮጵያ ጋር ደም ያፋሰሰ ጦርነት አካሂዳለች፡፡ ከጂቡቲ ጋርም ከሰኔ 3-6 ቀን /2000 ዓ.ም ተመሳሳይ ምክንያት ያዘለ ጦርነት ማካሔዷ አይዘነጋም፡፡ ከጂቡቲ ጋር ያለው ውዝግብ ዛሬም ድረስ በቋፍ ላይ ነው፡፡ ከሱዳን ጋር ያላት ግንኙነትም ሻክሯል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሱዳን ለደህንነቴ ታሰጋኛለች በሚል ከኤርትራ ጋር የምትዋሰንበትን ድንበር እስከ መዝጋት የደረሰ እርምጃም ወስዳለች፡፡ እነዚህና መሰል ጉዳዮች ሀገሪቱ ከጎረቤቷቿ ጋር የነበራት የሁለት አስርት ዓመታት ግንኙነት መልካም የሚባል እንዳልነበረ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ኤርትራ በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውን አልሻባብ ትደግፋለች በሚል ከሚቀርብባት ወቀሳ በተጨማሪ ከጂቡቲ ጋር ከምትወዛገብበት ድንበር ወታደሯቿን ለማስወጣት ፈቃደኛ ባለመሆኗ የተባበሩት መንግሥታት ታህሳስ 14 ቀን 2002 ዓ.ም የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ጥሎባታል፡፡ በመሪዎች ላይ የጉዞ እገዳን ጨምሮ የፖለቲካና ወታደራዊ መሪዎች ሀብት ንብረትም እንዳይንቀሳቀስ የሚያደርግ ማዕቀብ ተላልፎባታል፡፡ የሀገሪቱ ቀጠናዊና ዓለም ዓቀፋዊ ግንኑነት መሻከር ለሁለት አስርት ዓመታት ከዘለቀው የኢትጵያና ኤርትራ ግንኙነት መቋረጥ ጋር ተደማምሮ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገቷ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፏል፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት በኢትዮጵያ በኩልም ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡ ቢቢሲ የወቅቱን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጥናት ኢንስቲትዩት ሪፖርት ዋቢ አድርጎ ነሐሴ 1 ቀን 1993 ዓ.ም ያወጣው ዘገባ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት ተኩል በዘለቀው ጦርነት 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር አውጥታለች፡፡ ይህም ለጦርነቱ የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል፣ የቁሳቁስና መሰል አስፈለጊ ነገሮችን ለማንቀሳቀስ ጥቅም ላይ ስለመዋሉ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ በሪፖርቱ መሰረት ጦርነቱ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ የመሰረተ ልማት አውታሮችን አውድሟል፤ በአካባቢው የነበረውን የተረጋጋ ህይወትና ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴም አስተጓጉሏል፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል ለ20 ዓመታት የዘለቀው “ሞት አልባ ጦርነት” በባህል፣ በዘር ሀረግ፣ በቋንቋ፣… የተሳሰሩ ወንድምአማች ህዝቦች በአካል ብቻ ሳይሆን እንደ ስልክ ባሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችም ጭምር እንዳይገናኙ ጥቁር ነጥብ ጥሎ ቆይቷል፡፡ ሁለቱ ሀገራት ተደጋግፈው ማደግ ሲገባቸው በጠላትነት እየተፈራረጁ ዓመታትን መሻገራቸው ለሁለቱም ሀገራት ኪሳራ እንጂ ትርፍ አልነበረውም፡፡ ሀገራቱ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በመደጋገፍና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ባለመመስረታቸው ማግኘት የሚገባቸውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በሀገራቱ ድንበር አካባበቢ ያሉ ሰዎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶችንም ለማስፋፋት ካለመቻሉም በላይ አካባቢዎቹ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ውጭ ሌላ ገጽታ እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡ በድንበር አካባቢ ያሉ ዜጎች የበይ ተመልካች ሆነው ለመኖር ከመገደዳቸውም በላይ በአካባቢው ጦርነት ቢቀሰቀስ ቀዳሚ የጦርነቱ ሰለባ የሚሆኑት እነዚሁ ነዋሪዎች በመሆናቸው የእለት ከዕለት ህይወታቸውን በውጥረትና ጭንቀት ውስጥ ሆነው ለማሳለፍ ተገደዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት በጠላትነት መፈራረጅ እንዲያበቃና ሰላም እንዲወርድ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ቀጠናዊ ጥረቶች ቢደረጉም እርባና ያለው ውጤት ሳይመጣ 20 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሁለቱ ሀገራት ለሁለት ዓመታት ከግማሽ ያህል ያካሔዱት ጦርነት ያደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ለመግታት ሰኔ 11 ቀን 1992 ዓ.ም የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ለግጭቱ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ይቻል ዘንድ ደግሞ ታህሳስ 3/1993 ዓ.ም ሁለቱ ሀገራት የአልጀርሱን የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ይሁን እንጂ የሰላም ስምምነቱ በተለያየ ምክንያት ባለመተግበሩ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነገሰው ውጥረት ሳይረግብ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡበት ዕለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት በየፈርጁ የተከፋፈለ ታሪካዊ ንግግር ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በአጠቃላይ ከኤርትራ ጋር ደግሞ በተለይ ሊኖራት የሚገባውን ግንኙነት አመላክተዋል፡፡

ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃ ከልብ እንፈልጋለን፤ የበኩላችንንም እንወጣለን፡፡ በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለጽኩ የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪየን አቀርባለሁ፡፡

ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ ፓኬጅ ለመተግበር ዝግጁ መሆኗን ይፋ ሲያደርግ ህዝቡ ከኤርትራ በኩል ያለውን ምላሽ ለመስማት ተቻኮለ፡፡ የኤርትራን ምላሽና አቋም ለማወቅ 15 ቀናትን ለመጠበቅ ግድ ቢልም ሰኔ 13 ቀን 2010 ዓ.ም የተከበረውን የኤርትራ ሰማዕታት ቀን ምክንያት በማድረግ ፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ አፈወርቂ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው የኢትጵያን የሰላም ጥያቄ መቀበላቸውንና ውይይቱን ለመጀመርም ልዑካቸውን ወደ አዲስ አበባ እንደሚልኩ አበሰሩ፡፡ ይህን ባሉ በስድስተኛው ቀን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው የተመራው የኤርትራ ልዑክ የአዲስ አበባን ምድር ረገጠ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና አትሌቶች የሞቀ አቀባበል አደረጉለት፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በቤተ መንግሥት ለልዑኩ በተዘጋጀው የእራት ግብዣ ፕሮግራም ላይ “ከኤርትራውያን ወንድሞቻችን ጋር የሚያዋጣን ፍቅር ብቻ ነው፡፡ ጸቡን ሞክረነዋል፤ ለሁለቱም ወገን አክሳሪ ነው፡፡ ሰው፣ ጊዜ፣ ሀብት፣ ጭንቅላትም ይበላል፡፡ እንኳን ለፍቅርና ለእርቅ፣ ለጦርነትም ብዙ ዋጋ ስለከፈልን ለእርቅ ማንኛውንም ዋጋ ከፍለን ከኤርትራውያን ወንድሞቻችን ጋር ተደምረን ለማደግ ከፍተኛ ፍላጎት አለን” በማለት የመንግሥታቸውን ቁርጠኛ አቋምና ፍላጎት አረጋገጡ፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተጋረደው “ጥቁር መጋረጃ” መቀደዱንም አበሰሩ፡፡ ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁንና  የሁለቱን ምክር ቤቶች አፈጉባዔዎችን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎቻቸውን አስከትለው በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካኝነት የአስመራን መሬት በመርገጥ አንድም በሁለቱ ሀገራት መካከል የተከለለውን ጥቁር መጋረጃ ለሁለት ቀደዱ፤ በሌላ በኩልም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሰላም በሰላም አስመራ ውሮፕላን ማረፊያ እንዲያርፍ ምክንያት ሆነዋል፡፡ አስመራ ለኢትዮጵያ ልዑክ ባደረገችው አቀባበል በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል የነበረውን ጥልቅ ፍቅርና ናፍቆት ዓለም ተመልክቶበታል፡፡ ግዙፎቹ ዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙኃንም ይህን ታሪካዊ ክስተት ተቀባብለው ዘግበውታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይና የኤርትራው ፕሬዝዳንት በተገናኙበት ቅጽበት የተለዋወጡትን በፈገግታና በፍቅር የተሞላ ሰላምታ የዘገባዎቻቸው አካል በማድረግ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በጠላትነት ሲፈራረጁ የነበሩ ሀገራት ግንኙነታቸውን ለማደስ ቁርጠኝነታቸውን ባረጋገጡ ጥቂት ቀናት ውስጥ ያሳዩትን ተጨባጭ ለውጥ ከማስተጋባት አላመነቱም፡፡ ኤርትራውያን ከአውሮፕላን ማረፊያው እስከ አስመራ ቤተመንግሥት ድረስ በመንገዶቹ ግራና ቀኝ ተሰልፈው በእልልታና በጩኸት ለኢትዮጵያ ልዑክ ያደረጉት አቀባበል ለኢትዮጵያ ህዝብ ያላቸውን  ፍቅርና አክብሮት ስለማረጋገጡ እማኝ መጥቀስ አያሻም፡፡ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ትናንትን ለታሪክ ትተው ነገን ከዛሬ የተሻለ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስምምነቶችን በማድረግ የሁለቱን ሀገራት ተስፋ አለምልመዋል፡፡ ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ አፈወርቂ ከ20 ዓመታት በኋላ የአዲስ አበባን መሬት ረገጡ፡፡ የአዲስ አበባና አካባቢዋ ነዋሪ ስለሰላም በሰላም የአዲስ አበባን መንገዶች አጥለቅልቆ ፍቅሩን፣ አክብሮቱንና ናፍቆቱንም ሳይሰስት ገልጿል፡፡ የፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ የኢትዮጵያ ጉብኝትም በሁለቱ ሀገራትና ህዝቦች መካከል ጥቁር ነጥብ የጣለው "ጥቁር መጋረጃ" ሙሉ ለሙሉ ለመቀደዱ ትልቅ ማረጋገጫ ሆኗል፡፡ ፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ በተለይ በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው የሁለቱ ሀገራት የሰላም ማብሰሪያ መድረክ ላይ ከህዝቡ ለተቸራቸው ክብርና ፍቅር ደረታቸውን በሁለቱም እጆቻቸው ጥብቅ አድርገው በመያዝና በእጆቻቸው ከንፈሮቻቸውን እየሳሙም ጭምር ለህዝቡ ያላቸውን ፍቅር በፈገግታ ገልጸዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ በዚሁ ዝግጅት ላይ ንግግር ለማድረግ ወደ መድረክ ብቅ ሲሉ ከህዝብ የጠበቃቸው ፍቅርና ክብርም እጅጉን የተለየ ነበር፡፡ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግርም “ማንም…ማንም! ፍቅራችንን ለመበተንና ለማወክ፣… ልማትና እድገታችንን ለማደናቀፍና ለማውደም እንዲፈታተነን አንፈቅድም” በማለትም ለወዳጅ ጠላት የሁለቱን ሀገራት ቀጣይ ግንኙነት በግልጽ አብስረዋል፡፡ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሃዋሳ የተደረገላቸው አቀባበልም አግራሞትን እንዳጫረባቸው ከገጽታቸው ለመረዳት አዳጋች አልነበረም፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህሩ ዶክተር ጌታነህ መሀሪ “አብሮ ከመውደቅ አብሮ መነሳት” ለሁለቱም ሀገራት ጠቃሚ መሆኑን ገልጸው በተለይ በጠላትነት ሲፈራረጁ ሁለት አስርት ዓመታትን ለዘለቁት ሀገራት አሁን የተጀመረው አዲስ ምዕራፍ “ከፍተኛ ፈውስ” የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑም ሁለቱ ሀገራት ያለውጭ ጣልቃ ገብነት ከጥላቻና በጠላትነት ከመፈራረጅ ተላቀው አዲስ ምዕራፍ መጀመራቸው መልካም መሆኑን አንስተዋል፡፡ ግንኙነቱን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ከተፈለገ ሁለቱም ሀገራት ራሳቸውን ከጸብ ጫሪነት ማራቁ የመጀመሪያ እርምጃ ሆኖ ህዝቦቻቸውም በእርቀ ሰላሙ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማበረታታትና ማነቃቃት እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል፡፡ ፕሮፌሰር ካሳሁን እንዳሉት የሁለቱ ሀገራት መሪዎች “ተፈራርመው፣ ተጨባብጠውና ተቃቅፈው” መለያየታቸው ብቻውን የታለመውን ግብ አያመጣም፡፡ ይልቁንስ ስምምነቶቻቸውን በአሳሪ ውሎች እያጠበቁ የህዝቦችን ድጋፍና ተሳትፎ እያጎለበቱ መሄዱ ግንኙነቱን ዘላቂና ውጤታማም ያደርገዋል ባይ ናቸው፡፡ ጀነራል አበበ ተክለሃይማኖት በኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ የተለያዩ ጥናቶችን አድርገዋል፡፡ እርሳቸውም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማደስ የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነቱ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ህዝቡም ለጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሄዎችን የሚጠቁምበትን አማራጭ ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በጉዳዩ ላይ ምሁራንን ማሳተፉም መዘንጋት እንደማይኖርበት ነው ጀነራል አበበ ያስገነዘቡት፡፡ በቅርቡ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ኢዜአ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ አስተማሪና ተመራማሪው ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ እንዳሉት የሁለቱ ሀገራት መንግሥታት ድንበር የማካለሉን ስራ ጨምሮ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ስምምነቶችን ሲፈጽሙ በየደረጃው ያለውን ህብረተሰብ፣ ምሁራንን፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችን፣… ተሳትፎና ምክረ ሃሳብ መዘንጋት አይኖርባቸውም፡፡ በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ ተመሳሳይ ቋንቋ፣ ወግና ባህል የሚጋሩ ዜጎች እንደመኖራቸው መጠን ስምምነቶችና ውሳኔዎችም ጭምር የህዝቦችን ፍላጎትና የጋራ ተጠቃሚነት ታሳቢ አድርገው ከተፈጸሙ ህዝቡ ውሳኔዎቹና ስምምነቶቹም “የመንግሥት እንጂ የእኛ አይደሉም” የሚል ቅራኔ እንዳያነሳ ያደርጋል፡፡ የሁለቱን ሀገራት መሪዎች የኢትጵያና ኤርትራ ጉብኝት ተከትሎ በሀገራቱ መካከል ሰፍኖ የነበረው ውጥረት ረግቧል፡፡ የህዝብ ለህዝብና የምጣኔ ሀብት እንዲሁም የፖለቲካ ግንኙነቱም ሳይውል ሳያድር ተጀምሯል፡፡ ሁለቱም ሀገራት ግንኙነቶቻቸውን ማጠናከር እንዲችሉ ኤምባሲዎቻቸውን ከፍተዋል፡፡ በቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክም በኤርትራ ጉብኝት አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መደበኛ በረራውን ጀምሯል፤ የአሰብ ወደብም አገልግሎት መስጠት እንዲችል አስፈላጊው አድሳት ተደርጎለታል፡፡ በሀገራቱ መካከል ለዓመታት ነግሶ የቆየው ቂም በቀለኝነት፣ ጥላቻና በጠላትነት መፈራረጅ እንዲያበቃና ፍቅር፣ አንድነትና ትብብር እንዲጎለብት ያለሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት የተደረጉ ጥረቶችንና የተወሰዱ እርምጃዎችን ሀገራት በተናጠል ዓለም ዓቀፍ፣ አህጉራዊና ቀጠናዊ ድርጅቶችና የሃይማኖት ተቋማትም ጭምር አድናቆት ቸረዋቸዋል፡፡ ለሀገራቱ ግንኙነት ዘላቂነትም ድጋፍና አጋርነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ደግሞ በተለየ ሁኔታ የሁለቱ ሀገራት ሰላምና ጦርነት አልባ ግንኙነት እንዲሻሻል ሁለቱ መሪዎች ላበረከቱት አስተዋጽኦና ላሳዩት ቁርጠኝነት የሀገሪቱን ከፍተኛ የሲቪል ሽልማት አበርክታላቸዋለች፡፡ አሁን ጥቁር ነጥብ ጥሎ ያለፈው ጥቁር መጋረጃ ያለማንም ጣልቃ ገብነት በሁለቱ ሀገራት መሪዎች ቁርጠኝነት ተቀዷል፡፡ ማዶ ለማዶ እየተያዩ ለዓመታት የተራራቁ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦችም ዳግም መገናኘት ጀምረዋል፡፡ ጥቁሩ መጋረጃ ሳይፈለግና ሳያስፈለግ በሁለቱ ሀገራት መካከል ተሰቅሎ መቆየቱንም መጋረጃው በተቀደደባቸው ቀናት የሁለቱም ሀገራት ህዝበች ካሳዩት በፈገግታና እልልታ የተታጀበ ምላሽ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ያ ጥቁር መጋረጃ ከታሪክነት አልፎ ድጋሚ በሁለቱ ሀገራት መካከል ጥቁር ጥላውን እንዳያጠላ የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶችና ልዩ ልዩ ተቋማትም ጭምር በንቃት ሊጠብቁትና ለዘላቂነቱ መረጋገጥም የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም