የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዲጂታል የሲቪል ሰርቪስ መረጃ አያያዝ ስርዓት መተግበር ጀመረ

146

የካቲት 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞችን መረጃ በቴክኖሎጂ በታገዘ አሰራር ለመያዝ የሚያስችል የተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ መረጃ አያያዝ ስርዓት መተግበር ጀመረ።

የአሰራር ስርዓቱ ከሰራተኞች ቅጥር እስከ ስንብት ያለውን መረጃ በቴክኖሎጂ በመታገዝ መዝግቦ የሚይዝ ነው።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ እና ሌሎች የቢሮ ኃላፊዎች በተገኙበት የአሰራር ስርዓቱ የማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት የከተማዋ የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ ሉሌ እንዳሉት፤ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የተዘጋጀውን አገር አቀፍ የሰራተኞች መረጃ መመዝገቢያ ሶፍትዌር በከተማዋ ተግባራዊ ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል።

የአሰራር ስርዓቱ በሁሉም የከተማዋ ተቋማት የሚተገበር መሆኑን ገልፀው፤ "የሰራተኛ ቅጥርንና ሌሎች መረጃዎችን ለመከታተል ያስችላል" ብለዋል።

አሰራሩን ለመተግበር 13 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር መመደቡንም ተናግረዋል።

የመረጃ ስርዓቱ በከንቲባ ፅህፈት ቤት ምዝገባን በማካሄድ ስራውን በዛሬው እለት እንደጀመረና በቀጣይ ወደሌሎች ተቋማት እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

ተቋማት ለአሰራር ስርዓቱ ተግባራዊነት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም አሳስበዋል።

ከኢንተርኔትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አስረድተዋል።

በከተማዋ የተለያዩ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ የታገዙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ ናቸው።

የዲጂታል መታወቂያ እንዲሁም የንግድና ገቢ ስርዓትን ለማዘመን እየተከናወኑ ያሉ አሰራሮችን በማሳያነት አንስተዋል።

ቴክኖሎጂን የማልማትና ለማበልፀግ የሚሰሩ ተቋማት ቴክኖሎጂዎችን የማናበብ ስራ እንዲያከናውኑም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም