ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ ወጣቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

57

  አዲስ አበባ የካቲት 30/2013 ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ ወጣቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ለኢዜአ አስተያየት የሰጡ ሴቶች ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ ወጣቶች፤ ወላጆችና የፖለቲካ ፓርቲዎች በኃላፊነት እንዲንቀሳቀሱ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

በተለይም ወጣቶች ለሰላም ዘብ በመቆም ድርብ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሰው ሃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው ብለዋል።

ወይዘሮ ፈትያ ደድገባ ወጣቶች ከፍተኛውን የአገሪቱን ህዝብ ቁጥር የሚይዙ በመሆናቸው ቀጣዩ ምርጫ የወደፊት ራዕያቸውን በስፋት የሚያረጋግጡበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በመሆኑም ወጣቶች ይበጀናል የሚሉትን ፓርቲ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሊመርጡ ይገባል ብለዋል፡፡

ወጣቶች እኩይ ዓላማ ባላቸው ሃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ወላጆች ተገቢውን ኃላፊነት እንዲወጡም ነው ጥሪ ያቀረቡት።

ወይዘሮ መሳይ ንጉሴ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ከምርጫ ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ የሰላም መደፍረሶች ቀዳሚ ተጎጂዎች ወጣቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ሰላምን የሚያደፈርሱ ችግሮች እየተፈቱ በመምጣታቸው ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንደሚከናውን ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።

በምርጫው የሚወዳደሩ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ በሚያከናውኑበት ወቅት ወጣቶችን ወደ አላስፈላጊ ድርጊት የሚገፋፉ መልዕክቶችን ከማስተላለፍ መቆጠብ እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።

ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ከተከናወነ ወጣቶች የሚያነሷቸው የተለያዩ ጥያቄዎች የመፈታት እድል እንዳላቸው የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ሰሀራ መሀመድ ናቸው።

በመሆኑም ወጣቶች ምክንያታዊ በሆነ መልኩ በመንቀሳቀስ ለሰላም መስፈን ዘብ እንዲቆሙም ጠይቀዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ወጣቶችን በማሳተፍ ረገድ ብዙ መስራት እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም