በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገጾች በሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ላይ ኀብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል

48
አዲስ አበባ ሀምሌ 20/2010 በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገጾች በሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ ኀብረተሰቡ ወደ ግጭትና ብጥብጥ እንዳይገባ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ። የአገሪቱን ሰላም የሚያደፈርሱ ኃይሎች የሚያሰራጯቸውን የሐሰት መረጃዎች በመከተል አገራችን ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንዳትገባ ኀብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል። በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ሰላም ወዳድ ባልሆኑ ኃይሎች በሚቀሰቀሱ ግጭቶች በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው። በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገጾች የሚተላለፉ የተሳሳቱ መረጃዎች ግጭቶች እንዲባባሱ የሚያደርጉ በመሆናቸው ሰላም ወዳዱ ኀብረተሰብ መረጃውን በሰከነ መንፈስ ሊረዳው ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ኀብረተሰቡ የሚነሱትን ጥያቄዎች በሥርዓትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በማቅረብ ከአላስፈላጊ ግጭትና ሁከት ራሱንና አካባቢውን ሊጠብቅ እንደሚገባ ገልጸዋል። በአገሪቱ ያለውን ሰላም ለማስቀጠል ሁሉም የኀብረተሰብ ክፍል በጥቅማ ጥቅም ሳይደለልና እኔን አይመለከተኝም ሳይል የበኩሉን ግዴታ መወጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል። የከተማው ነዋሪ አቶ ክፍሉ ለማ በአስተያየቱ"አሁን ያለውን ሰላም በአግባቡ መጠቀም መቻል አለብን ፀረ ሰላም ሀይሎች ውስጣችን ገብተው እርስ በእርሳችን ለማናቆር ለማጣላት የሚያደርጉትን ፕሮፓጋንዳ አገናዘበን አይተን የትኛው ነው ጥሩ ያልሆነው ብለን መያዝ አለብን። ˝ ብሏል፡፡ " በእርግጥ ሰላም ለሁሉም ነው የመጣው ሰላምን የማይፈልግ የለም ግን ጥቅማቸውን የተነካባቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ስለዚህ እነሱ የሚያመጡት ነው አንዳንዶች የሚቀሰቅሱትን ቅስቀሳ አይተናል  ህበረተሰቡ ጎጂው የቱ ነው ጠቃሚው የቱ ነው የሚለውን አስቀድመው ተገንዝበው ለእዚህ ነገር ባይሰለፉ በተለይ አንዳንድ ወጣቶች ለእዚህ ለእኩይ ተግባር ሰላምን ለሚያደፈርስ ነገር ˝ ይገባል ያሉት አቶ ክፍሉ ለማ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱትን ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ በመፍታት የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት እንዳይደርስ ማድረግ ተገቢ እንደሆነም ተናግረዋል። የአገሪቱ ህዝቦች በልዩነት ውስጥ አንድ ሆነው ለዘመናት የኖሩ ሲሆን ከቀደምት አባቶች የወረስነውን የአብሮ መኖርና የመከባበር ባህል ማስቀጠል ይገባል ብለዋል። ኀብረተሰቡ ለልማት፣ለመልካም አስተዳደርና ለሌሎች ጥያቄዎች ምላሹን በትዕግስት መጠበቅና የሰላም ዋጋ የማይተመን መሆኑን መገንዘብ እንዳለበትም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም